
ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በመቄት ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት የወባ መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ ሰለሞን አስፋው በወረዳው በአምስት ቀበሌዎች የወባ በሽታ መከሰቱን ገልጸዋል። የበሽታ ክስተቱ ባለፉት ዓመታት ከነበረው በሰባት እጥፍ የጨመረ መኾኑንም አብራርተዋል።
የወባ መከላከያ ኬሚካል መረጨት የነበረባቸው ቀበሌዎች በኬሚካል እጥረት ምክንያት አለመረጨቱንም ነው አቶ ሰለሞን የገለጹት።
ኅብረተሰቡ የወባ መራቢያ ቦታዎችን እንዲያጸዳ የማስተባበር ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ሰለሞን በሽታው ወደ ወረርሽኝ እንዳያድግ ለመከላከልም ኾነ ለማከም ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ሲስተር ፈለቁ መኮነን በዞኑ 16 ሺህ 273 የወባ ታማሚና ምልክቶች የተመዘገበ መኾኑን ገልጸዋል። ከባለፈው ዓመትም ከፍተኛ ጭማሪ እንዳለው ነው የጠቀሱት።
ባለፉት ዓመታት የነበረው የወባ ክትትልና መከላከል ሥራ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ደካማ መኾኑና ዘንድሮም በተከሰተው ግጭት ምክንያት የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ በሚፈለገው ልክ ባለመሠራቱ ለበሽታው በስፋት መከሰት ምክንያት እንደኾነ ነው ሲስተር ፈለቁ የተናገሩት።
በሁለት ወረዳዎች የኬሚካል ርጭት መካሄዱን እና የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ መኾኑን የጠቀሱት ኀላፊዋ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ግን በሚፈለገው ልክ ለመሥራት አስቸጋሪ እንደኾነ አስገንዝበዋል፡፡ ኾኖም በቅርብ በሚገኙ ባለሙያዎችና ከዚህ ቀደም በቀረበው መድኃኒት እንዲጠቀሙ እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ሲስተር ፈለቁ ከክልል ጤና ቢሮ እና ሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር በሽታው እንዳይሰፋ እየተሠራ ነውም ብለዋል። ወረዳዎች ያለባቸውን ጊዜያዊ የግብዓትና መድኃኒት እጥረት ከምሥራቅ አማራ መድኃኒት አቅራቢ ድርጅት እንዲወስዱ መመቻቸቱንም ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ የወባ መራቢያ ቦታዎችን በማጽዳት፣ አጎበርን በመጠቀምና የባለሙያ ምክርን በመተግበር ራሱን ከወባ በሽታ እንዲከላከል ሲስተር ፈለቁ አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!