
ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሥራቸውን በመደበኛነት እንዲጀምሩ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መኾኑን አቶ ደሳለኝ ጣሰው ደሳለኝ ጣሰው ገልጸዋል፡፡
በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም ችግር ምክንያት በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ለመቀበል መቸገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ አብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ለመቀበል ዝግጅት ቢያደርጉም የሰላም ዋስትና እስኪያገኙ ድረስ ተማሪዎችን ለመጥራት እንቸገራለን ብለው ነበር፡፡ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ግብዓቶችን ለሟሟላት መቸገራቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ እና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው የክልሉን ሰላም በተሟላ መልኩ በመመለስ ወደ መደበኛ የሥራ እንቅስቃሴ ለመመለስ እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙባቸው ከተማዎች ሰላም መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ ዩኒርሲቲዎች ሥራ እየጀመሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ ተማሪዎችን እንዳይጠሩ የሰላም ችግር አንደኛው ምክንያታቸው ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ የመንገዶች ዝግ መኾን የግብዓት አቅርቦት በፈለጉት መንገድ እንዳያቀርቡ ችግር ኾኖባቸው መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች ሙሉ ዝግጅት እንዲያደርጉ የገበያ እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴው የተሟላ መኾን እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡ ነጻ እንቅስቃሴ ተገድቦ በመቆየቱ ተማሪዎችን ጠርቶ ለማስተማር ችግር እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ ችግሮችን እየተሻገሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲዎች በራሳቸው መርኃ ግብር መሰረት ተማሪዎችን ጠርተው ትምህርት መስጠት የሚችሉበት እድል እንዳለም ገልጸዋል፡፡ የነበረው ችግር ተሻሽሎ እየተቀየረ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ዪኒቨርሲቲዎች ግብዓት ለማቅረብ ሲቸገሩበት የነበረውን ነጻ የትራንስፖርት እቅስቃሴ ችግር እየፈታን ነው ብለዋል፡፡ ችግሮች እየተፈቱ እንደሚቀጥሉ እና ዩኒቨርሲቲዎችም ሥራቸውን በመደበኛነት እንደሚሠሩ ነው የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!