
ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ እንደ ማንኛውም የዓለም ሀገራት መልክዓ ምድር፣ ሕዝብ፣ ባሕል፣ የተፈጥሮ ሃብት፣ ታሪክ እና ፖለቲካ ባለቤት ናት። ለየት የሚያደርጓት ቀለሞች እና ማንነቶችን የታደለች ሀገር ናት።
ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ ዕድሜ እና የራሷ ፊደል እና ቋንቋ ያላት፣ የልዩ የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት ባለቤት፣ እስልምናና ክርስትናን ቀድማ ተቀብላ አቻችላ ያኖረች፣ የቀደምት ሥልጣኔ ባለቤት፣ ቅኝ ገዥዎችን የደቆሱ የነጻነት ቀንዲል ሕዝቦች ምድር፣ ተዘርዝረው የማያልቁ የተፈጥሮ፣ የታሪክ፣ የሕል፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የጥበብ፣ የፍልስፍ እሴቶች ባለቤት ናት።
ፈተናዎቿ ቢበዙም በእምነት፣ በጽናት እና በመረዳዳት ችግርን የሚያልፉ፤ ደረታቸውን ለጦር እግራቸውን ለጠጠር ሰጥተው የሚጠብቋት አራት አይና መሪዎች እና ቀናኢ ልቦና ያላቸው ሕዝቦች እናት ምድር ናት ኢትዮጵያ። በዘመናት ሂደት በዓለም ላይ የመንግሥታት መውደቅ እና መነሳት፣ የኃያላን የጉልበት መለካካት ነጻነቷን እና ሕልውናዋን ቢፈትነውም በብልህ መሪዎቿ እና በተባባሪ ሕዝቦቿ ስሟ ሲቀደስ እና ሲወደስ፤ ሰንደቋ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ እስከዛሬው ዘመን ደርሳለች።
ዛሬም ፈተና መልኩን ቀይሮ አንዱ ባንዱ ላይ ተነባብሮ ለሌላ ድል እና ታሪክ እየፈተናት ይገኛል። ምዕራባውያን የቀደምት ሥልጣኔ ባለቤትነቷ፣ የነጻነት ተምሳሌትነቷ የእግር እሳት የኾነችባቸውን ኢትዮጵያን ሲሻቸው ጦር አዝምተው ለመውረር፣ አሊያም በፖለቲካ ሴራ ሕዝቦቿን እርስ በርስ ለማጋጨት እንቅልፍ አይወስዳቸውም። ቢቻል የተበታተነች እና አቅመ ቢስ ሀገር ማድረግ፣ ካልኾነም በእርስ በርስ ግጭት ለማኝ እና ተረጂ፣ በማንነቱ የሚያፍር ሕዝብ ለመፍጠር አመቺ ጊዜ እየጠበቁ መፈተናቸው ቀጥለዋል።
መልኩን የቀየረው የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፈተናዋም ሕዝቧቿን በብሔር አና በሃይማኖት ልዩነት በማጋጨት ዳኛም ቀማኛም የመኾን የምዕራባውያን ሴራ ነው። ይህን በውል ባለመረዳትም ኾነ ለግል ጥቅማቸው እና ፍላጎታቸው ሲሉ ግጭቶችን የሚያባብሱ የብሔር እና የሃይማኖት ፖለቲከኞች ደግሞ ችግሩን በፈረስነት መጎተታቸው ፈተናውን ከባድ አድርጎታል።
አንድነቷን እና ነጻነቷን ጠብቃ መኖሯ እረፍት የነሳቸው አውሮፓውያን አንዱን ጨቋኝ ሌላውን ተጨቋኝ፣ አንዱን ሥልጡን ሌላኛውን ኋላቀር፣ አድርገው የሠሩት ከፋፍሎ የማጋጨት ሴራ ዛሬ ላይ ጎልምሶ ፈተናነቱ አይሏል።
ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ መንግሥት የተከተለው ብሔር ተኮር የመንግሥት መዋቅር ደግሞ በስመ ፌዴራሊዝም ሕዝቦችን እርስ በርስ እያኮራረፈ እና እያነቃቀፈ፣ አንዱን አንበሳ ሌላውን ኮሳሳ በሚያደርግ ከፋፋይ ትርክቶቹ በመንግሥት ዕውቅና ተሰበከ። ሕዝቦች በቂም ተኳረፉ፤ በጉልበት ተገፋፉ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግን የሥልጣን ወንበራቸውን አስፋፉ። ዜጎች መርጠው ባልተወለዱበት ማንነት ተፈናቀሉ፤ ተገደሉ። የውጪ ወራሪ ሲመጣ ሆ! ብለው የሚዘምቱት ኢትዮጵያውያን መልኩን ቀይሮ የመጣባቸውን የህልውና አደጋ ግን ክፉኛ ሲፈትናቸው ታየ።
በብዙኀን መገናኛዎች የሚተላለፉት የግጭት እና የጥፋት መልዕክቶች፣ የጉምቱ ”ፖለቲከኞች” እና ”ምሁራን” በብሔር እና በሃይማኖት ከለላ የግል ጥቅምን በማሳደድ አንዱን ቀድሰው ሌላውን አርክሰው ለግጭት መቀስቀሳቸው ሌላው የኢትዮጵያ ፈተና ክብደት ማሳያ ነው።
ከመመካከር ይልቅ መፎካከር፣ ከመከባበር ይልቅ መናናቅ የበዛበት የወቅቱ ፖለቲካ ማንም ይጠንስሰውና ያዘጋጀው ተዋናዮቹም ተጎጂዎቹም ራሳቸው ኢትዮጵያውያን ስለኾኑ የችግሩ መፍትሔም ራሳቸው ናቸው።
ለመኾኑ ዜጎችን ለስደት እና ለውርደት የዳረገ ድህነት፤ ድህነቱን የወለደውን የሰላም እጦት መንስኤ ውጤቱ እና የመፍትሄ ብልሃቱ ምንድን ነው? ኢትዮጵያውያን በነጠላ ትርክት ተጠምደው ለልዩነት እና ግጭት የዳረጋቸው ምንጭ እና ከችግሩ መውጫ መንገዱስ ምንድን ነው?
በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ ማብሬ ታዴ ሃሳባቸውን ሰጥተውናል።
ኢትዮጵያ በዓለም ታሪክ በሊግ ኦፍ ኔሽን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምስረታ፣ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበርም ንቁ ተሳታፊ እንደኾነች ይጠቅሳሉ። እንደ አክሱም፣ ጎንደር እና ላሊበላ ያሉ ቅርሶችን ለዓለም በማበርከትም በሥልጣኔ አሉ ከሚባሉ ሀገራት ውስጥ እንደኾነችም ያክላሉ።
ይሁን እንጂ በፖለቲካው ዘርፍ ሥልጣንን በኃይል ብቻ የመንጠቅ የፖለቲካ ባሕላችን የተበላሸ ነው ሲሉ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አብራርተዋል። በፍጹም የበላይነት እና አሸናፊነት ላይ የተመሰረተ ባሕልን ይዞ የቆየው የኢትዮጵያ ፖለቲካ መረጋጋት አጥቶ መቆየቱም ለአሁናዊ ችግሮቻችን እርሾ ኾኖ ማገልገሉን መምህሩ አውስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ”ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ከፋፋይ ትርክት አንዱ አባባሽ ነገር ነው” ብለዋል። በሕንድ ከ120 በላይ ብሔሮች ተቻችለው በመኖር በዓለም አምስተኛ ኢኮኖሚ መገንባታቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ ”ነጠላ እና የተዛባ ትርክት ሀገር አይገነባም” በማለት ኢትዮጵያውያን በነጠላ እና የተሳሳተ ትርክት ለችግር መዳረጋቸውን አመላክተዋል።
አቶ ዮሴፍ ገብረ ሚካኤል በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጥናት መምህር እና ተመራማሪ ናቸው። ኢትዮጵያ የብዝኀነት ሀገር መኾኗን አውስተው በእንዲህ አይነትት ሀገር ፌዴራሊዝም የመንግሥት አወቃቀር ችግር አይደለም ይላሉ።ችግር የሚኾነውም አለመከባበር እና አለመቻቻልን ማረቅ ካልተቻለ ነው ብለዋል።
የመረዳዳት፣ የመከባበር፣ የእንግዳ ተቀባይነት እና መሰል ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን ለመሸርሸራቸው አንዱ ምክንያት ሀገሪቱ የምትከተለው የመንግሥት አወቃቀር መኾኑን ጠቅሰዋል። ሰዎች በጥፋታቸው እንዳይጠየቁ ብሔርን መሸሸጊያ የማድረግ የሥርዓት ብልሽት እንደሚታይም አንስተዋል።
የፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ መዋቅር ውስንነቶች እየተመጋገቡ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ”የኔ ብቻ ነው ትክክል” ባይነት የነጠላ ትርክት የፖለቲካ ችግር እንዳደረሷት ነው ምሁሩ የደመደሙት። ማኅበረሰቡን ለሞት እና መፈናቀል ከዳረጉት አሁናዊ ችግሮች መካከል በጉልሁ ተጠቃሽ መኾኑንም ይጠቅሳሉ።
ችግሮች ዓለም አቀፋዊ ሊኾኑም እንደሚችሉ የጠቀሱት መምህር ዮሴፍ “ካፒታሊዝም ሥርዓት የራሱ የኾነ ጫና አለው፤ ፊልሙ፣ ቴሌቪዥኑ፣ ማኅበራዊ ሚዲያው እና የመሳሰሉት ቴክኖሎጂ የወለዳቸው የምዕራባውያን የግንኙነት ባሕሎች ማኅበራዊ መስተጋብሮቻችን እየሸረሸሩ ነው” ብለዋል። በሌላ በኩል የመቻቻል፣ የመተጋገዝ እና አብሮ የመኖር ባሕሎቻችን ብሔርን ለግል ፍላጎታቸው ብቻ በሚጠቀሙ ስግብግብ ሰዎች በሂደት መሸርሸራቸውን ነው መምህር ዮሴፍ የገለጹት።
የጋራ ትርክቶቻችን የተዳከሙ ቢመስሉም ወቅታዊ እንጂ ጨርሰው አለመጥፋታቸውን ያናገርናቸው ምሁራን ይጋራሉ። ብሔርተኛ ፖለቲከኞች በሚዲያ ከሚያሰራጩት ከፋፋይ ትርክት ውጭ አብዛኛው ሕዝብ ተከባብሮ እና ሠርቶ ከማደር ያለፈ አጀንዳ የለውም ብለዋል። ከፋፋይ ትርክቶቻችንን ከነአካቴው በመተው እና አንድ የሚያደርጉንን የጋራ ትርክቶቻችንን ደግሞ በማጎልበት የታፈረች እና የተከበረች የጋራ ሀገር መገንባት እንደሚያስፈልግም ምሁራኑ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
