“የሚያለያየንን በማረም እና በመተው፣ አንድ የሚያደርገንን ደግሞ በመውሰድ ታላቅ ሀገር መገንባት ይገባል” ደሳለኝ ጣሰው

38

ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ልዩነቶችን በማስፋት በሚፈጠር ቅራኔ ሀገር ሰላም ስታጣ ቆይታለች፡፡ አሁንም በሰላም እጦት ላይ ናት፡፡ ልዩነትን እንደ ጌጥ በመቆጠር አንድነትን ማስቀደም እና በአንድነት መኖር ደግሞ ታላቅ ሀገር እንድትኖር ያደርጋል፡፡ አንድነት ታላቅ ሀገርን አቆይቷል፡፡

በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ እና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው በአማራ ክልል የተፈጠረውን የሰላም እጦት በዘላቂነት ለመፍታት ከሕዝብ ጋር ሰፋፊ ውይይቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሕዝብን የምናወያዬው የተቀየመባቸው ችግሮች ምንድን ናቸው፣ ዛሬ የሚፈቱት፣ ነገ እና ከነገ ወዲያ የሚፈቱትስ የትኞቹ ናቸው ብሎ ቆጥሮ ለማወቅ ነው ብለዋል፡፡ ከሕዝብ ጋር የሚደረጉ ውይይቶች የሕዝብን ጥያቄዎች በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ለመፍታት የሚያስችሉ ግብዓቶች የሚወሰዱባቸው መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ሕዝብ የጸጥታ ችግር ገጥሞታል፤ ይሄ የታወቀ ጉዳይ ነው፣ ችግሮችን ግን በግጭት መፍታት አይቻልም ብለዋል፡፡ ከሕዝብ ጋር እየተደረጉ ባሉ ውይይቶች ጥያቄዎች ምንድን ናቸው? ጥያቄዎችስ የሚፈቱት በሰላም ነው ወይስ በሌላ መንገድ የሚለው እንደሚነሳም አመላክተዋል፡፡ የጥያቄዎች መፍቻ መንገድ ሰላማዊ አማራጮች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በሕዝብ ዘንድ የዋሉ ያደሩ፣ በዕቅድ የተያዙ ጥያቄዎች አሉ ያሉት አቶ ደሳለኝ መሠረታዊ ጥያቄው የመልካም አሥተዳደር መሆኑንም አንስተዋል፡፡

እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው አሥተዳደራዊ ሥራዎች ቀልጣፋ፣ ታማኝ እና ለሕዝብ ቀና የሆነ አገልግሎት በመስጠት በኩል ሰፊ ችግር መኖሩ በሕዝብ ዘንድ የሚነሳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሥስተዳደራዊ መዋቅሩ ያሉ ሌብነት እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ሕዝብን ያማረሩ ስለመሆናቸውም በሕዝብ ውይይቶች የሚነሱ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በጊዜ እና በፍጥነት አይፈቱም፣ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ አያገኙም፣ የተጀመሩ የልማት ተቋማት በፍጥነት እና በጥራት አይጠናቀቁም፣ የቀበሌ መታወቂያ ለማውጣት እንኳ ያለው ሌብነት እና ውጣ ውረድ ቀላል የሚባል አይደለም፣ ለሕዝብ ጀሮ ስጡ የሚለው የሕዝብ ጥያቄ ትልቁን ሥፍራ የሚይዘው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ይሄ ጥያቄም ዘላቂ የመፍቻ መንገድ አድርገን የምንወስደው እና ውስጣችንን የምናይበት ነው ብለዋል፡፡ የሕዝብን ጥያቄዎች መፍታት እንደሚገባ ቁርጠኝነት ተውስዶ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በሕዝብ ውይይቶች እንደ ሀገር የሚፈቱ ጥያቄዎች እንደሚነሱም አመላክተዋል፡፡ ድህነት፣ ሥራ አጥነት እና ሌሎች ጥያቄዎችም በሕዝቡ ዘንድ በስፋት የሚነሱ ጉዳዮች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ ፈጣን እና ተወዳደሪ ትውልድ የመፍጠር ኀላፊነት የመሪ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ሰላም ሲመጣ የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች መመለስ እና ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ ሕዝብን እያማረረ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት በውስጥ አቅም መፍታት አንደኛው ቁልፍ ሥራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ለዜጎች መቃቃር ምክንያት የሚሆኑ ሀገራዊ አጀንዳዎች እንደሚነሱ የተናገሩት አቶ ደሳለኝ ለብቻ ተሠርተው የማይመለሱ የሕዝብ ጥያቄዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡ የጋራ ትብብርን እና ወንድማማችነትን የሚጠይቁ የአማራ ሕዝብ አንኳር ጥያቄዎች እንዳሉም ተናግረዋል፡፡ ዜጎች በየትኛውም የሀገራቸው ክፍል ኮርተው እና ሠርተው ያለምንም ስጋት እንዲኖሩ ማድረግ፤ ማዶና ማዶ ሆነው የሚተያዩ፣ አንዱ አንደኛውን የሚያሳድድበት እንዳይሆን መሠራት አለበትም ብለዋል፡፡ ሰው በመሆናቸው ብቻ ተከብረው፣ ባይታዋር ሳይሆኑ እኩል ተሳስበው፣ በኢትዮጵያዊነታቸው ኮርተው እንዲኖሩ ምቹ ሥርዓትን መፍጠር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

የሕዝብን አንድነት የሚያጠናክሩ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ደሳለኝ ለዓመታት የቆዩ ጥያቄዎችን በአንድ ጊዜ እና በአንድ ጀንበር መፍታት እንደማይቻልም አመላክተዋል፡፡ ነገር ግን ይላሉ አቶ ደሳለኝ የሕዝብን አንድነት የሚያናጋ፣ ከፋፋይ እና የሚያለያይን አስተሳሰብ በማረም አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ ለዜጎች ዋስትና የሚሰጥ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊው ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችን ለመፍታት እና መሻሻል የሚገባቸውን ሁሉ ለማሻሻል በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ተስፋ እንዳለው ያነሱት አቶ ደሳለኝ በአማራ ክልል ሊኖሩ የሚችሉ አጀንዳዎችን የሚለይ ኮሚቴ ወደ ሥራ መግባቱንም ገልጸዋል፡፡ እንደ ሀገር የልዩነት ምክንያት የሆኑትን ወደ አንድነት ለማምጣት እድል እንደሚኖርም ተናግረዋል፡፡ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በርካታ ጥያቄዎች እና መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች ሊታረሙ እንደሚችሉም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ለነገ የሚጠቅመን ምንድን ነው? ዛሬ ላይስ የሚያለያዬን የትኛው ነው? የሚለውን በመለየት የሚያለያየንን በማረም እና በመተው፣ አንድ የሚያደርገንን ደግሞ በመውሰድ ታላቅ ሀገር መገንባት ይገባልም ብለዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ የዘመናት ጥያቄ የሆኑ የማንነት እና የወሰን ጥያቄዎች ዘላቂ እና አስተማማኝ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ የዜጎችን አብሮነት በማይሸረሽር መልኩ ለመፍታት በጥንቃቄ እየተሠራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች አጀንዳ ሆነው በዘላቂነት እንዲፈቱ በቁርጠኝነት እየሠራን ነውም ብለዋል፡፡

የዜጎችን መፈናቀል በዘላቂነት ለማስቆም እና ችግሮችን ለመፍታት በልዩነት ሳንሳሳብ በአንድነት መሥራት አለብንም ብለዋል፡፡ የዜጎችን መፈናቀል እንዳይኖር ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች በቁርጠኝነት እየተሠሩ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንጂ በግጭት ለመፍታት ማሳብ የበለጠ እንደሚያወሳስባቸውም አመላክተዋል፡፡

መፍቻ መንገዱ ሰላም እና ውይይት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በሕዝብ ስም ተገቢ ያልሆነ አካሄድ መሄድ እና የሕዝብን ጥያቄ ባልተገባ መንገድ ለመፍታት መነሳት አዋጭ አለመሆኑንም አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከሸኔ ጋር በሁለት ዙር ሲካሄድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት ተቋጭቷል።ከሸኔ ጋር በሁለት ዙር ሲካሄድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት ተቋጭቷል።
Next article“ትርክት እና ኢትዮጵያዊነት”