ከሸኔ ጋር በሁለት ዙር ሲካሄድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት ተቋጭቷል።ከሸኔ ጋር በሁለት ዙር ሲካሄድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት ተቋጭቷል።

164

ሰላምና መረጋጋት የአንድ ሀገር ልማትና ብልጽግና መሠረት ነው።

ልዩነቶችን በስክነትና በሠለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት የመፍታት ባህል ከማዳበር ውጭ የሚገኝ ሰላም፣ የሚጎለብት አብሮነት አይኖርም። የኢፌዲሪ መንግሥት ከዚሁ እምነቱ በመነጨ አቋም የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት፣ የፖለቲካ ፕሮግራም ከማይጋሩት ፓርቲዎች ጋር የመንግሥትን ሥልጣን ተጋርቷል።

በዚህም ከመገዳደል በመለስ የሚካሄድ የምርጫ ሥርዓትና የሀገር አስተዳደር ልምምድ ለማዳበር፣ ነፍጥ አንሥተው ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ሥልጣን ለመያዝ ከሞከሩትም ጋር በተደጋጋሚ በውይይትና በሰጥቶ መቀበል መርሕ ሰላምን ለማስፋት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፤ በማድረግ ላይም ይገኛል።

በመንግሥት በኩል ሕገ መንግሥቱንና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመቀበል ዝግጁ ከሆነ ከማንኛውም ኃይል ጋር በውይይት ችግሮችን ለመፍታት ያለማሰለስ ጥረት ይደረጋል።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከመከላከያ ትይዩ የሚታይ ትጥቅ የመያዝ፣ በመንግሥት ውስጥ መንግሥት የመሆን ልክፍትን ግን በውይይት ሽፋን መለማመድ አደገኛ ሀገር አፍራሽ አዝማሚያ ነው ብሎ ያምናል።

በመሆኑም መንግሥት ተገዶ የገባበትን ግጭት ለማስቆም ያለማሰለስ ርምጃ በመውሰድ ሀገር የማጽናት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን ይወጣል።

በዚሁ አግባብ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አከባቢዎች በመንቀሳቀስ በሕዝቦች ሕይወትና ንብረት ጉዳት በማድረስ የሰላም ጠንቅ ሆኖ ከቆየው የሸኔ የሽብር ቡድን ጋር በታንዛንያ ዛንዚባር ከወራት በፊት ውይይት ተካሂዶ ሳይቋጭ መቅረቱ ይታወሳል።

በዚሁ ውይይት ወቅት የሽብር በድኑ ከ60 ዓመታት በፊት የኦሮሞም የሌሎች የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችም ሁሉ ጥያቄዎች የነበሩና ተመልሰው ያደሩ ጥያቄዎችን አንሥቷል። በተለይም ከለውጥ በኋላ በሥራ ላይ የዋሉ ጉዳዮችን ከማነብነብ ውጭ የሚቆጠርና የሚቋጠር አጀንዳ ማምጣት ስላልቻለ በመንግሥት በኩል በስክነትና በማግባባት ላይ ብቻ ታጥሮ በቀጠሮ ተንጠልጥሎ እንዲቆይ ማድረጉ ተመራጭ አካሄድ ነበር።

ባለፉት ሁለት ሳምንታትም የሽብር ቡድኑ ከባለፈው ስሕተት ተምሮ የድርድር ነጥቦቹንም ሀገሪቱ ከደረሰችበት ምዕራፍ ጋር ለማጣጣም ይሞክር ይሆናል በሚል ተስፋ ሁለተኛ ዙር ውይይት ታንዛንያ ዳሬ ሰላም ላይ ሲካሄድ ቆይቷል። በሽብር ቡድኑ ዘንድ በዚህኛው ዙርም “መንግሥት አዝሎ መንግሥት ያድርገኝ” ከሚል አጉራ ዘለልነት ያለፈ የድርደር ነጥብ ማምጣት አልቻለም።

ነገር ግን በኢፌዲሪ መንግሥት በኩል በሀገሪቱ ሰላም ሰፍኖ ኢትዮጵያ ያሉዋትን ጸጋዎች ወደ ተጨባጭ ሀብትና አቅም ቀይራ ብልጽግናዋን ታረጋግጥ ዘንድ ካለው ጉጉት በመነጨ ከግማሽ መንገድ በላይ ተጉዞ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ሞክሯል። ነገር ግን የሽብር ቡድኑ በሰላም ጊዜ እንዴት መኖር እንዳለበት ለማሰብ ቸግሮት ታይቷል።

በዜጎች ደምና እንግልት መነገዱን መርጧል። በመሆኑም ውይይቱ በዛሬው ዕለት ያለ ውጤት ተበትኗል። የኢፌዴሪ መንግሥት ለሰላማዊ መፍትሔ ያለው አቋም እንደተጠበቀ ሆኖ ሕግና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የማስከበር ተልዕኮውን አጠናክሮ ይቀጥላል።

በዚሁ አጋጣሚ ውይይቱ እንዲሳካ ጥረት ሲያደርጉ ለነበሩ አካላት ሁሉ ምስጋና ያቀርባል።

ህዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ
የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

Previous article“አንድ የሚያደርገንን ገመድ ቋጥረን መያዝ አለብን” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“የሚያለያየንን በማረም እና በመተው፣ አንድ የሚያደርገንን ደግሞ በመውሰድ ታላቅ ሀገር መገንባት ይገባል” ደሳለኝ ጣሰው