
ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሥልጠናቸውን ሲወስዱ የነበሩ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ሥልጠና የማጠቃላያ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል።
በማጠቃላያ ሥነ ሥርዓቱ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የርእሰ መሥተዳደሩ የሕዝብ ግንኙነትና የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ ይርጋ ሲሳይ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሚኒስትር መለስ ዓለሙን ጨምሮ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ የሥልጠናው ዓላማ የትናንትናውን ችግር በመቅረፍ እና ያሉንን ጸጋዎች በመጠቀም ታላቋን ኢትዮጵያ ለመገንባት ነው ብለዋል።
በሥልጠናው በተገኘው ግብዓት ሀገራችንን ለመለዋጥ እና ለማሳደግ የምንተጋ መኾን ይገባናል ነው ያሉት። መለያየት ሕዝብና ሀገርን ዋጋ እንደሚያስከፍልም ገልጸዋል። ሀገርን ለማሳደግ መዘናጋት ሊኖር እንደማይገባም አመላክተዋል።
“አንድ የሚያደርገንን ገመድ ቋጥረን መያዝ አለብንም” ብለዋል። ሕዝብ በማኅበራዊ ትስስር መተሳሰር ሲገባው ትስስሩን የሚያናጉ ጉዳዮች መኖራቸውን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ ነፃ እንቅስቃሴ እና የሕዝብ ትስስር እንዲኖር መሥራት ይገባልም ብለዋል።
ሀገርን ለማሳደግ እና የተሻለች ለማድረግ አንድነትን በማጠናከር መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል። ሕዝብን በኢኮኖሚ እና በሌሎች መስኮች ማስተሳሰር ይገባልም ብለዋል።
ሠልጣኞች በሰላም እንዲሠለጥኑ ላደረጉ የጸጥታ ኃይሎች እና መልካም የእንግዳ አቀባበል ላደረጉ ሁሉ አመስግነዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!