“የአማራ ክልልን መልካም እሴት ከመንገር ባለፈ በምትሄዱበት ሁሉ የክልልን ሕዝብ እና መንግሥት እንደምታግዙ እተማመናለሁ” አቶ ይርጋ ሲሳይ

40

ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሥልጠናቸውን ሲወስዱ የነበሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሥልጠና የማጠቃላያ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል።

በማጠቃላያ ሥነ ሥርዓቱ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የርእሰ መሥተዳደሩ የሕዝብ ግንኙነትና የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ ይርጋ ሲሳይ፣ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሚኒስትር መለስ ዓለሙን ጨምሮ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በማጠቃላይ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የርእሰ መሥተዳደሩ የሕዝብ ግንኙነትና የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ ይርጋ ሲሳይ ኢትዮጵያ ትበለፅጋለች እንጂ ለአንድ አፍታም ሸብረክ አትልም ብለዋል። ኢትዮጵየዊነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እድል በማግኘታችን ደስተኞች ልንኾን ይገባናል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያዊነት ጥልቅ መሠረት፣ ጥልቅ መንፈስ እና ጥልቅ ምስጢር ነው ብለዋል። ከአባቶቻችን የተቀበልናትን ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስረከብ ይገባልም ብለዋል። በሥልጠናው የተገኘውን አቅም መሬት ላይ በመቀየር ሀገርን የማሳደግ ተልዕኮ ይጠብቀናል ነው ያሉት።

ወደአማራ ክልል ስትመጡ ስጋት ሊኖርባችሁ እንደሚችል ይታወቃል ያሉት አቶ ይርጋ በኢትዮጵየዊነት የሚያምን ክልል ሕዝብ እንዳያችሁ እተማመናለሁ ብለዋል።

በክልሉ በብዙ አካባቢዎች ሰላም ኾኖ መደበኛ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል። የአማራ ክልልን መልካም እሴት ከመንገር ባለፈ በየሄዳችሁበት ሁሉ የክልሉን ሕዝብ እና መንግሥት እንደምታግዙ እተማመናለሁ ብለዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበባሕር ዳር ሥልጠና እየወሰዱ የሚገኙ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ።
Next article“አንድ የሚያደርገንን ገመድ ቋጥረን መያዝ አለብን” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ