“በጦርነት የሚፈታ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የለም” የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን

43

ደሴ: ኅዳር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን በመካነ ሰላም ከተማ በወቅታዊ የሰላምና የጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል። መንግሥት በቁርጠኝነት ከሕዝቡ ጋር በቅንጅት መሥራት አለበት ሲሉም አሳስበዋል።

የሀገር ሽማግሌና የሃይማኖት አባቶች ጦር አንግበው ጫካ የገቡትን መክረው ለሰላማዊ ውይይት በማምጣት ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ሲሉም ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

በጸጥታ ችግር ምክንያት የመማር ማስተማር ሥራው ከፍተኛ እክል እንደገጠመው ተናግረዋል። ህፃናትና ታዳጊዎች በዚህ ሰዓት የትምህርት ቤት ደጃፍን አልረገጡም ሲሉ ገልጸዋል።

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚመለሱት ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር እንደሆነ የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠቁመዋል። ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ተገቢውን ክብር መስጠት ያሻልም ነው ያሉት።

በተለያዩ አካባቢዎች በነፃነት የመንቀሳቀስ እጦት፣ የተጋነነና ወቅቱን ያላገናዘበ ግብር፣ የሕገ መንግሥት ጉዳይ፣ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች በውይይቱ ላይ ከተነሱት ጉዳዩች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳደሪ አሊ መኮንን የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች ዘላቂ እልባት ለመስጠት በመንግሥት በኩል በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። ጥያቄውን ሽፋን በማድረግ ክልሉን የትርምስ ቀጣና ማድረግ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል።

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ማስመለስ የሚቻለው በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር ኅብረ ብሔራዊነትን በጠበቀ መንገድ በሕግና በሥርዓት ብቻ ነው ብለዋል ዋና አሥተዳዳሪው።

የደቡብ ወሎ እና የደሴ ከተማ ኮማንድ ፓስት ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄነራል ዘውዱ ሰጥአርጌ ኅብረተሰቡ ሐሰተኛ መረጃ ሰምቶ ከመደናገር ራሱን መጠበቅና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ የበኩሉን መወጣት አለበት ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ጀማል ይማም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሁሉም አካል ሰብዓዊነትን ያስቀድም” የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን
Next articleበባሕር ዳር ከተማ ሥልጠናቸውን ሲወስዱ የነበሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት እየተከናወነ ነው።