
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ጠየቀ።
በአማራ ክልል በድርቅ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ኮሚሽኑ በክልሉ ከሚገኙ ዞኖች ጋር ውይይት አድርጓል። ችግሩን ለተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችም ማቅረቡን ገልጿል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ከሚሽን ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የገንዘብ እና የምግብ እህል ድጋፍ አድርጓል ብለዋል። አጠቃላይ ከተመደበው የምግብ እህል 60 በመቶው መቅረቡን ነው ያነሱት።
ኮሚሽነሩ እንዳሉት ክልሉ ካለው የእህል ክምችት ለ1 መቶ 11 ሺህ ተጠቃሚዎች ተደራሽ ተደርጓል፤ የክልሉ መንግሥት በመደበው አንድ መቶ ሚሊዮን ብር የምግብ እህል ተገዝቶ በመጓጓዝ ላይ ይገኛል፤ በክልሉ ከሚገኙ ልማታዊ ድርጅቶች በተገኘ ድጋፍ 9 ሺህ 470 ኩንታል የምግብ እህል ችግሩ በከፋባቸው የሰሜን ጎንደር ዞን እና የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ተደራሽ እየኾነ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡ መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች በተገኘ 205 ሚሊዮን ብር ለእንስሳት መኖ እና የምግብ እህል ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ዩኒቨርሲቲዎችም ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጅ በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር የተመደበውን ምግብ እህል ለማድረስ እና የጉዳቱን መጠን ተንቀሳቅሶ ለማጥናት አስቸጋሪ አድርጎታል። አርሶ አደሮች የማምረት ሥራቸውን እንዳያከናውኑ፣ ችግር ውስጥ የወደቁ ዜጎችን ተንቀሳቅሶ ድጋፍ ለማድረግ እና እንስሳትንም ግጦሽ እና ውኃ ወዳለበት አካባቢ ለማንቀሳቀስ ፈታኝ መኾኑን ገልጸዋል።
ክልሉ ያጋጠመው ችግር ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የሚያሥፈልግ እንደኾነ ያነሱት ኮሚሽነሩ የመንግሥት ተቋማት፣ የእርዳታ ድርጅቶች እንዲኹም በውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!