”የህፃናትን ችግር ለመቅረፍ ሁሉም ኅብረተሰብ መተጋገዝ ይኖርበታል” የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ

42

ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 34ኛው የዓለም ሕፃናት ቀን በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በሚገኘው ግሬስ የሕፃናት እና ቤተሰቦቻቸው መርጃ ማዕከል ተከብሯል።

”ለዛሬዎቹ ሕፃናት ፍቅር እና በጎነት እናውርስ” በሚል መሪ ቃል ነው በዓሉ የተከበረው። በዝግጅቱ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለመገንባት ሕፃናት ላይ መሥራት አስፈላጊ ነው ብለዋል። ከተማ አሥተዳደሩ ይህን በመገንዘብ በሕፃናት ልማት ላይ ለሚሠሩ እንደ ግሬስ ላሉ ተቋማት እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

የግሬስ ሕፃናት ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ወርቁ አሳብ ማዕከላቸው ለሕፃናትን የመዋያ፣ የትምህርትና ወላጆቻቸው የጠፉባቸውን የማሳደግ አገልግሎት እየሰጠ መኾኑን ገልጸዋል። ”ሕፃናትን ስናስብ ሀገር ነው የምናስበው ሁሉም አካል የሕፃናት ጉዳይ ይመለከተናል ብሎ ነገን የሚረከብን ትውልድ ዛሬ ላይ መቃኘት አለበት” ብለዋል። ሕፃናት በደህንነት እና በስነ ምግባር እንዲያድጉ ሁሉም ጊዜና ቦታ ሳይመርጥ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ወይዘሮ ዝና ጌታቸው በክልሉ በድርቅ እና በግጭት ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን የመርዳ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል። ”በሕፃናት ላይ እየደረሰ ያለው ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ችግር መቅረፍ ለበጎ አድራጊዎች ብቻ የሚተው አይደለም፤ ሁሉም ማኅበረሰብ መተጋገዝ ይኖርበታል” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ በ6ኛው የአፍሪካ ፍርድ ቤቶች የጋራ የውይይት መድረክ እየተካፈለች ነው።
Next article“ሁሉም አካል ሰብዓዊነትን ያስቀድም” የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን