
ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በአልጀርስ ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው 6ኛው የአፍሪካ ፍርድ ቤቶች የጋራ ውይይት መድረክ እየተሳተፈች ነው።
በመክፈቻ ፕሮግራሙ የአልጅሪያው ፕሬዚዳንት አብዱልመጅድ ተቡኔ በተወካያቸው አማካኝነት መልእክት አስተላልፈዋል። በመልእክታቸው አልጀሪያ ለአፍሪካ ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሥራ እድገት ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
የአፍሪካ ኀብረት የአፍሪካን ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዳኛ ኢማኒ ዳውድ አቦድ ውይይቱ በክልል እና በሀገር ውስጥ ፍርድ ቤቶች መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር የሰብአዊ መብት ጥበቃን ለማጎልበት እና ለዳኞች እና የሕግ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ እና ሙያዊ ማሻሻያ ቦታዎችን በመፈተሽ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት የሕግ ዳኝነትን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በ6ኛው የአፍርካ ፍርድ ቤቶች ጉባኤ የኢትዮጵያ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህርት፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ ዋና ጸሐፊ ደሳለኝ ወይሳ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ.ር) ኢትዮጵያን ወክለው እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የውይይት መድረኩ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ይኾናል። ይህ መድረክ በአፍሪካ ፍትሕና ሰብአዊ መብቶችን ለማስፈን በክልላዊ እና በሀገር ውስጥ ፍርድ ቤቶች፣በሕግ ባለሙያዎች እና በባለድርሻ አካላት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!