
ደብረ ብርሃን: ኅዳር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአሲዳማነት የተጠቁ መሬቶችን በኖራ በማከም ምርትና ምርታማነት ማሳደግ መቻሉን የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ገልጿል። ዞኑ ተራራማነት የሚበዛበት አካባቢ በመኾኑ በዝናብ አማካኝነት ለም አፈሩ ሰለሚታጠብ እና ሌሎች አጋላጭ በኾኑ ምክኒያቶች መሬቱ ለአሲዳማነት እየተጋለጠ ይገኛል ተብሏል።
በዞኑ የሚገኙ 13 ወረዳዎች ለመሬት አሲዳማነት የተጋለጡ ስለመኾናቸው ተገልጿል። የአንጎለላና ጠራ ወረዳ ከእነዚህ መካከል ተጠቃሽ ነው። በወረዳው ካሉ 16 ቀበሌዎች ውስጥ 9ኙ በአፈር አሲዳማነት የተጠቁ ናቸው።
የአንጎለላና ጠራ ወረዳ ሰብል ልማት ቡድን መሪ መሰረት ቀጸላ በ2015/16 የመከር ምርት ዘመን 100 ሺህ ኩንታል ኖራ በመጠቀም በተለይ የቢራ ገብስ እና ስንዴ ሰብል በመዝራት ምርትን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል። ከዚህ በፊት የሚመረተውን ምርት በእጥፍ ማሳደግ እንደተቻለ በሰብል ግምገማ ወቅት ተረጋግጧል ነው ያሉት።
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሰሎሞን ቀለሙ በዞኑ በአሲዳማነት ተጋላጭ ከኾኑ አካባቢዎች 185 ሄክታር መሬት ላይ ናሙና ተወስዶ በኖራ የማከም ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ችግሩ የከፋ እና አስቸኳይ መፍትሄ የሚፈልግ ቢሆንም የኖራ ዋጋ እና አቅርቦት እየፈተናቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ምክትል ኀላፊው የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀም የጥራጥሬ እህል መዝራት እና የሰብል ተረፈ ምርቱን መሬቱ ላይ እንዲበሰብስ በማድረግ የአፈር ለምነትን ለመመለስ እየተሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!