
ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን 190 ሺህ ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ ሰሊጥ ወደ ማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታውቋል። የመምሪያው ኀላፊ አቶ ጌትነት በሪሁን እንደተናገሩት በዚህ ዓመት 980 ሺህ ኩንታል የሰሊጥ ምርት በሕጋዊ መንገድ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሠራ ነው።
በዚህም ባለፈው አንድ ወር በተደረገ የሰሊጥ ግብይት እንቅስቃሴ 190 ሺህ ኩንታል በሕጋዊ አቅራቢ ነጋዴዎች እና ድርጅቶች ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል። ምርቱ በ28 አንደኛ ደረጃ የገበያ ማዕከላት በሚያቀርቡ 500 አቅራቢዎች፣ አቀናባሪዎች እና በአምራች ባለሃብቶች መሰረት የተከናወነ መኾኑን ጠቁመዋል።
ለማዕከላዊ ገበያ የቀረበው የሰሊጥ ምርት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ110 ሺህ ኩንታል ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል። ባለሃት አርሶ አደሮች በሰሊጥ ምርት ላይ በስፋት በመሰማራቱና የተሻለ ምርት በመመረቱ እንደሆነ አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ ያለውን የሰሊጥ ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የተያዘውን እቅድ ሙሉ በሙሉ ለማሳካትም በሕገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ አካላትን የመቆጣጠሩ ጉዳይ ትኩረት እንደተሰጠውም አስገንዝበዋል።
የሮዝ ስታር ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ የሺወርቅ ተገኘ እንዳሉት ድርጅታቸው ወደ ማዕከላዊ ገበያ የቀረበ ሰሊጥን በመግዛት ወደ ውጭ ይልካል።
በዚህ ዓመት ከ6 ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ ወደ ውጭ ለመላክ አቅደው እየተንቀሳቀሱ ሲሆን እስካሁንም ከ4 ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ ከማዕከላዊ ገበያ በመግዛት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
ጥራት ያለው የሰሊጥ ምርት በበቂ መጠን እየቀረበ መሆኑንም አመላክተዋል። በሕገ ወጥ መንገድ እየተፈጸመ ያለ ግብይት ሀገሪቱ የምታገኘውን ገቢ እያሳጣ በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባው ተናግረዋል።
በመተማ ወረዳ በኮኪት አንደኛ ደረጀ የገበያ ማዕከል አቅራቢ ነጋዴ አቶ ተካልኝ ይብለጥ በበኩላቸው “በዚህ ዓመት የተገኘው ሰሊጥ በጥራትም ይሁን በብዛት ካለፈው አመት የተሻለ ነው” ብለዋል።
በዚህ ዓመት እስከ 2 ሺህ ኩንታል ሰሊጥ ለማቅረብ ማቀዳቸውን ገልፀው እስካሁን የ500 ኩንታል ሰሊጥ ግብይት መፈፀማቸውን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በዞኑ ባለፈው ዓመት ከ470 ሺህ ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ እንደተቻለም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!