“በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር የድርቅ ተጎጅዎችን ለመደገፍ የሚሠራውን ሥራ አስቸጋሪ አድርጎታል” ዲያቆን ተስፋው ባታብል

50

ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት የተከሰቱ ተደራራቢ ችግሮች ማኅበረሰቡን ለችግር እንዲጋለጥ አድርገውታል፡፡ በተለይም ደግሞ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተከሰተው ጦርነት 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቅሎ እንደነበር የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን መረጃ ያሳያል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በክልሉ በ2015/16 የምርት ዘመን በተከሰተው ድርቅ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለችግር ተጋልጧል፤ በእንስሳት ላይም ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

በክልሉ ዘጠኝ ዞኖች፣ አርባ ሁለት ወረዳዎች እና በ425 ቀበሌዎች ላይ ድርቅ መከሰቱን ያነሱት ኮሚሽነሩ በዋናነት በተከዜ ተፋሰስ ችግሩ እንደሚጎላ ገልጸዋል፡፡

በሰሜን ጎንደር ዞን ጃናሞራ፣ በየዳ እና ጠለምት ወረዳዎች፣ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰሃላ፣ ዝቋላ እና አበርገሌ ወረዳዎች፣ በማዕከላዊ ጎንደር ምዕራብ እና ምሥራቅ በለሳ እና ኪንፋንዝ በገላ ወረዳዎች፣ በደቡብ ጎንደር መቀጠዋ ወረዳ፣ በሰሜን ወሎ ራያ፣ ሀብሩ እና በከፊል ጉባላፍቶ ወረዳዎች፣ በደቡብ ወሎ ደግሞ አርጎባ እና ተንታ ወረዳዎች የከፋ ችግር እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

በአጠቃላይ በክልሉ ከ1 ሚሊዮን 846 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለችግር ተጋልጠዋል፡፡ ሕጻናት፣ እናቶች እና አረጋውያን ደግሞ ይበልጥ ተጋላጭ ኾነዋል፡፡ እንስሳት ላይም ጉዳት መድረሱን ኮሚሽነሩ አንስተዋል፡፡ መረጃው በቀጣይ ሊጨምር እንደሚችልም ነው የገለጹት፡፡

“በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር የድርቅ ተጎጅዎችን ለመደገፍ የሚሠራውን ሥራ አስቸጋሪ አድርጎታል” ሲሉም ተናግረዋል። በመኾኑም ሁሉም የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ነጻ እንቅስቃሴን መፍቀድ እና ለተቸገሩት መድረስ ያስፈልጋል ብለዋል።

ዘጋቢ፡-ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በክልሉ የተከሰቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
Next article“ምዕራብ ጎንደር ዞን 190 ሺህ ኩንታል የሰሊጥ ምርት ወደ ማዕከላዊ ገበያ አቅርቧል” የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ