“በክልሉ የተከሰቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

64

ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከል በሚሠሩ ሥራዎች ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው። በውይይቱ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መልካሙ አብቴ(ዶ.ር) እና ሌሎችም ባድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በውይይቱ በክልሉ የተከሰቱ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው መሠራት እንዳለባቸው ተመላክቷል። በውይይቱ ላይ ማብራሪያ ያቀረቡት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች አማካሪ አዲሱ ጋሽነት በተለይ የኢንቨስትመንት ቦታዎች እና ትርፍ አምራች ወረዳዎች ላይ ወባ በሥፋት የሚታይባቸው አካባቢዎች መኾናቸውን ተናገረዋል። በ58 ወረዳዎች የወባ በሽታ ምልክቶች ታይተዋል፣ በ30 ወረዳዎች ደግሞ የክልሉን 75 በመቶ የሚሸፍኑ ሕሙማን የሚገኝባቸው ናቸው ብለዋል። ክልሉ ባሠራው ጥናት መሰረት በክልሉ የተከሰተውን የወባ እና የኮሌራ በሽታ ለመቆጣጠር እየተሠራ መኾኑን ያመላከተው ሪፖርቱ አሁን ምሥራቅ አማራ ላይ ድጋሜ መከሰቱ አመላክቷል።

በክልሉ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ተፈናቃዮች እንደሚገኙም ተናግረዋል። በክልሉ ተጠልለው ለሚገኙ ተፈናቃዮች የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል። የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እንቅፋት የኾኑ ነገሮች መኖራቸው ተጠቁመዋል። በክልሉ የተከሰተው ድርቅ ችግሩን እንዳሰፋውም አመላክተዋል፡፡

በክልሉ ያለው ሰላም እጦት ድጋፍ አድራጊ አካላት ተንቀሳቅሰው ለመሥራት እንዳላስቻላቸውም ገልጸዋል፡፡ የሕክምና ግብዓት እጥረትም ሌላኛው ፈተና መሆኑ ነው የተመላከተው፡፡ የሞባይል ኢንተርኔት መቋረጥ መረጃዎች ከወረዳዎች ለማግኘት መቸገር ችግሩን ሊያሰፋው እንደሚችል ተጠቁሟል።

ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሙሉዓለም የአማራ ባሕል ማዕከል በዓለም ባሕልና ሙዚቃ ፌስቲቫል ኢትዮጵያን ወክሎ ሊሳተፍ ነው።
Next article“በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር የድርቅ ተጎጅዎችን ለመደገፍ የሚሠራውን ሥራ አስቸጋሪ አድርጎታል” ዲያቆን ተስፋው ባታብል