ሙሉዓለም የአማራ ባሕል ማዕከል በዓለም ባሕልና ሙዚቃ ፌስቲቫል ኢትዮጵያን ወክሎ ሊሳተፍ ነው።

32

ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሙሉዓለም የአማራ ባሕል ማዕከል በሕንድ ሀገር በሚካሄደው 7ኛው የዓለም ባሕልና ሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ ሊሳተፍ መኾኑን ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ገልጿል።

ከኅዳር 13/2016 ዓ.ም ጀምሮ ለአስራ ሁለት ቀናት ያህል በሚካሄደው ፌስቲቫል ማዕከሉ 16 የሚደርሱ የኪነ-ጥበብ ሙያተኞችን ይዞ የሚሳተፍ ይኾናል። በአራት የሕንድ ከተሞች የኢትዮጵያን ባህል፣ ኪነ-ጥበብና እሴቶች የማስተዋወቅ ስራ ይሠራል።

የኢፌዲሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ ጥበብ፣ ስነ ጥበብና ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማኻዲ መድረኩ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሀገሮች ጋር ግንኙነት በማድረግ በኪነ ጥበቡ ዘርፍ እንደ ሀገር ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል። “የአማራ ክልል በችግር ውስጥ ሆኖ ሀገርን መወከል መቻሉ፤ በችግር ውስጥም ሀገርን መወከል እንደሚቻል ማሳያ ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ እና የልዑክ ቡድኑ መሪ ዶክተር አየለ አናውጤ

የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቻችን በሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሙዚቃዎችና ውዝዋዜዎች ላይ በቂ ዝግጅት አድርገዋል ብለዋል። ይህም የሀገራችንን ባሕል ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አዲሱን መጽሐፍ በአጭር ቀናት ውስጥ እናዳርሳለን” የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ
Next article“በክልሉ የተከሰቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት