
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አዲሱ ፍኖተ ካርታ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር መተግበር ከጀመረ ሁለተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል።ይሁን እንጂ አዲሱ መጽሐፍ ከተማሪዎች እና ከመምህራን እጅ ባለመድረሱ በተማሪዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማድረሱን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ወፍላ ወረዳ የመንከሬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና መምህራን ተናግረዋል።
ተማሪ ዘውዲቱ አብርሃ የ8ኛ ክፍል ተማሪ ናት። አዲሱ መጽሐፍ ያልደረሳት በመኾኑ የሚኒስትሪ ፈተናዋ ላይ ተጽዕኖ እንደፈጠረባት ገልጻለች።
መጽሐፉ ስላልደረሰ በሞባይላቸው እያስተማሩን ይገኛሉ ፤ባትሪያቸው ከዘጋ መማር ማስተማሩ ይቋረጣል በማለት የተናገረው ደግሞ ተማሪ አበራ ጸጋይ ነው።
የት/ቤቱ ርእሰ መምህርት አሰፉ አማረ የግብዓት እጥረት ቢኖርም ችግሩን ተቋቁመን መማር ማስተማሩን ቀጥለናል፤ ለሚመለከተው አካልም ችግሩን አሳውቀን መፍትሄ እየጠበቅን ነው ብለዋል።
የወፍላ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ሰሎሞን ተካ ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመቅረፍ እየሠሩ እንደሆነ ገልጸዋል። የመጽሐፍቱን ግብዓት እየጠበቅን እንገኛለን ብለዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የትምህርት መምሪያ ኃላፊ ሰይፉ ሞገስም አዲሱን መጽሐፍ በአጭር ቀናት ውስጥ ለወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች እናዳርሳለን ብለዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በቅርቡ በሰጠው መግለጫ ከ7ሚሊየን 462ሽህ በላይ አዲስ መጽሐፍትን ማከፋፈሉን ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!