“ግጭት የሚያጠፋው የሰውን ሕይወት፣ የሚበላው ኢኮኖሚን፣ የሚያቋርጠው ኢንቨስትመንትን ነው” ደሳለኝ ጣሰው

48

ባሕር ዳር: ኅዳር11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለጠንካራ ሀገር ጠንካራ ሰላም ያሥፈልጋል፡፡ ጠንካራ ሰላም ሲኖር ደግሞ ጠንካራ ምጣኔ ሃብት እና ጠንካራ ተቋማት ይኖራሉ፡፡ በሀገር ላይ ግጭት በበረከተ ዘመን የሰው ሕይወት ይጠፋል፤ ንብረት ይወድማል፤ የዜጎች ማኅበራዊ ሕይወት በእጅጉ ይናጋል፡፡ በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም እጦት ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ተገድበው ቆይተዋል፡፡ ያልተገቡ ፕሮጋንዳዎች እና የበረከቱ ሀሰተኛ መረጃዎች ደግሞ ግጭትን እያባባሱ፣ ሰላምን እያደበዘዙ ሲሄዱ ይታያሉ፡፡

በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ እና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው በአማራ ክልል ላይ ከፍተኛ የኾነ ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ እንደሚነዛበት አሥታውቀዋል፡፡

ከውስጥም ከውጭም ሰውነትን ዝቅ የሚያደርጉ ፕሮፓጋንዳዎች በሥፋት እንደሚሰራጩ ተናግረዋል፡፡ የሰው ሕይወትን በማሳጣት የሚገኝ ትርፍ ጊዜያዊ ካልኾነ በስተቀር ረብ የሌለው መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ለራስ ጥቅም እና ዝና ሲሉ ብቻ ዜጎችን በአልተገባ ፕሮፓጋንዳ ማጋጨት አክሳሪ አካሄድ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡

የክልሉን ሰላም የማይፈልጉ ወገኖች በሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ችግር እንደሚፈጠርም ገልጸዋል፡፡ የሚነዙ ፕሮፓጋንዳዎች ሀገር የማፍረስ አጀንዳ ያላቸው መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳዎች ሕዝብን እንደሚያደናግሩም ገልጸዋል፡፡

ሕዝባችን ሚዛናዊ ዕይታ ስላላው እንጂ እንደተነዙት ፕሮፓጋንዳዎች እና በሬ ወለደ ወሬዎች ቢኾን ኖሮ ሀገር የሚባል አይኖርም ነበር ብለዋል፡፡ የሀገር ሃብት እና መመኪያ የኾነውን ተቋም የአንድ አካል ማድረግ፣ የተከበሩ የሃይማኖት አባቶችን ማዋረድ፣ ያልተባለውን እና ያልታሰበውን እንደተባለ አድርጎ ማቅረብ፣ ሕዝብን ጥያቄዎችህን እንዳታነሳ ልትደረግ ነው እያሉ በሥፋት ማወናበድ በሥፋት የሚስተዋሉ ጉዳዮች መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ሀገርን ወደ ፊት ማራመድ የሚችል ሥራ መሥራት ብልኾች የሚያከናውኑት ከባድ ተግባር ነው፤ ሀሰተኛ ነገሮችን አንስቶ ሕዝብን ማደናገር ግን ነገን የማያስቡ ሰዎች የሚፈጽሙት ቀላል ነውር ነው ብለዋል፡፡ እንደ ቀላል የሚነዙት ፕሮፓጋንዳዎች እና ሀሰተኛ ወሬዎች ግን መዘዛቸው ከባድ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ለእውነታ እና ሕዝብ የሰጠውን አደራ ለመወጣት የሚጥርን መሪ እንዲገደል፣ እንዲሸማቀቅ ማድረግ የተለመደ የፕሮፓጋንዳ መንገድ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ለእውነት እና ለሰላም የሚጥሩ አባቶችን ክብር መንካት፣ ማዋረድ እና ማዋከብ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡ የሚነዙ ፕሮፓጋንዳዎች ወሰን እና ልክ እንደሌላቸው ያመላከቱት አቶ ደሳለኝ ፈጣሪ የመረጣቸውን የሃይማኖት አባቶችን ጭምር እንደማያከብሩ ነው የገለጹት፡፡

ሀሰተኛ አካሄዶችን መቀየር የሚቻለው ከእውነታ ጋር በመጋፈጥ እና ቀድሞ ለማኅበረሰብ በማሳወቅ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ለሕዝብ መረጃ መሥጠት እና በራሱ ሚዛን ላይ እንዲቆም ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ለሕዝብ ትክክለኛ እና ሚዛናዊ የኾኑ መረጃዎችን መሥጠት አሥፈላጊው ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ሚዲያዎች ሕዝባዊ ወገንተኝነትን በማስቀደም ለሕዝብ ትክክለኛ እና ሚዘናዊ መረጃዎችን ማድረስ ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡

ራስን ለመገንባት፣ ለመታወቅ እና አንደኛውን በማንኳሰስ እና ሌላኛውን ለማሞገስ የሚደረጉ አካሄዶች የተገቡ አለመኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በአማራ ክልል አሁን ላይ ያሉ መሪዎች ለሕዝብ ሲሉ በሀቀኝነት ላይ ቆመው እውነቱን እውነት፣ ሀሰቱን ሀሰት እያሉ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ችግሮችን በጋራ ነው የምንፈታቸው፣ የምንፈታቸው ደግሞ ሕዝብን ይዘን ነው የሚል አቋም ይዘው እየሠሩ መኾናቸውን ነው የገለጹት፡፡

የማኅበራዊ ሚዲያ እድገት እና ለውጥ ጥሩ ቢኾንም ሚዛናዊ ያልኾኑ ሀሳቦችን በማቅረብ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ በመኾኑ መመርመር ተገቢ ነውም ብለዋል፡፡

በሕዝብ ውይይቶች እውነተኛ መረጃዎችን አስቀድሞ ማሳወቅ እና ሕዝብ በራሱ ሚዛን ላይ እንዲቆም ማድረግ እንደሚገባ ትምሕርት የወሰዱበት መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ሰላም ከአንድ ወገን ብቻ የሚጠበቅ አይደለም ያሉት አቶ ደሳለኝ የክልልን እና የሀገር ሰላምና ደኅንነት የማስከበር ድርሻ የመንግሥት ቢኾንም ከእያንዳንዱ ዜጋ ሰላም ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ሁሉም ዜጋ ስለ ሰላም የማሰብ፣ ስለ ሰላም የመሥራት እና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ልምድን ማዳበር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ሁሉም ስለ ሰላም መሥራት ይገባዋልም ብለዋል፡፡ የትኛውም አካል የሰላም ዘብ መኾን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ሀገር የሚያሻግር ሀሳብ ለማምጣት ሰላም እንደሚያሥልግም ተናግረዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ለሰላም የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡ በክልሉም ኾነ ከክልሉ ውጭ ያሉ ወገኖች ለሰላም አስተዋጽዖ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ማኅበራዊ ሚዲያዎች ለሚያሥተላልፉት መረጃ ሚዛናዊነትን እና እውነትን ማስቀደም እንደሚገባቸው ያነሱት አቶ ደሳለኝ ለቁስ ካደርን፣ አዕምሮአችንን ከሸጥን፣ ሀገር እና ሕዝብን ማየት ካልቻልን ግጭትን በቀላሉ መጥመቅ ይቻላል ነው ያሉት፡፡

“ግጭት የሚያጠፋው የሰውን ሕይወት፣ የሚበላው ኢኮኖሚን፣ የሚያቋርጠው ኢንቨስትመንትን ነው” ብለዋል፡፡ ግጭት ለእድገት ብቻ ሳይኾን ለማኅበራዊ ትስስር ፈታኝ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ግጭት የሚቀሰቅሱ፣ አንድ የማያደርጉ፣ አንዱ አንዱን የሚገፋ አሥተሳሰብ እና የፖለቲካ ጫና በሚዛን አይቶ ማስተላለፍ አንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ለሕዝብ የሚጠቅምን መረጃ ማስተላለፍ እንደሚያሥፈልግም አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከቡሪኪና ፋሶ ጋር ያደርጋል።
Next article“ልምዶችን በመቀያየር የሚሠሩ የልማት ሥራዎች ለውጤት ያበቃሉ” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ