44ቱ ጎርጎራ እና ደብረሲና ማርያም

113

ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ በጎርጎራ ከተማ ጣና ሐይቅ ዳርቻ ላይ የምትገኘዉ ጥንታዊቷ እና ታሪካዊቷ የደብረሲና ማርያም አንድነት ገዳም ከ700 ዓመታት በላይ አስቆጥራለች፡፡
የቤተክርስቲያኗ ግድግዳ ከኖራና ድንጋይ የተሠራ ሲሆን ክዳኑ ሳር የለበሰ ነው፡፡ ከአንድ ወጥ አንጨት የተሠሩ 12 በሮች፣ 8 መስኮቶች እና 29 ዓምዶች አሉት፡፡

የበሯ ግዙፍ ጣዉላዎችና የምሶሶዎቹ ጠንካራነት ምን ያክል ጥንቃቄ እንደተደረገ ብልሃት ከጥበብ ጋር ያቆራኘ እንደኾነ ሕንፃዋ ማሳያ ነዉ።
ገዳሟ ከባሕር ዳር ከተማ ተነስቶ በጣና ሐይቅ ላይ በጀልባ 96 ኪሎ ሜትር በመቅዘፍ ወይም በጎንደር በኩል በየብስ ትራንስፖርት 240 ኪሎ ሜትር ተጉዞ ይደረሳል፡፡ ወደ ጎርጎራ ደብረሲና ማርያም አንድነት ገዳም በሁለቱም አማራጮች መጓዝ ይቻላል ማለት ነው፡፡

ዙሪያዋ በዕድሜ ጠገብ የፍራፍሬ ዛፎች የተከበበ ነው፡፡ ሰርክ ልምላሜ ወደማይለየው የደብረሲና ማርያም ገዳም ቅጥር ግቢ ሲገባ እጅግ ውብና ጸጥታ የሰፈነበት ስፍራ ነው፡፡
ዘመን በተሻገረ ባህላዊ ጥበብ የታነጸችው የደብረሲና ማርያም ገዳም የውስጥ ግድግዳ ላይ ስዕሎቿ የተመራማሪዎችን ቀልብ እንደሳቡ ዛሬን ደርሰዋል፡፡

ጎርጎራ እና አካባቢው በርካታ ታሪካዊ የኾኑ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ያሏትና በዙሪያዋ ከሰባት በላይ ገዳማት በጣና ደሴት ላይ ይገኛሉ።

የአፄ ሱስንዮስ ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ ቀልብን ከሚገዛ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ጋር ሲታይ አካባቢው በደን ከመሸፈኑ ጋር ተደማምሮ የብርቅዬ አእዋፋት መናኸርያ እንዲኾን አድርጎታል፡፡ ለዕይታ ማራኪ እና የበርካታ ታሪክ ባለቤት የኾነችው የደብረሲና ማርያም ገዳም በተለያዩ ጊዜያት የሥልጣን በትር የጨበጡ የነገሥታት አጽም፣ እልፍ ጉዳዮች የተከወኑባቸው ቁሳቁሶች፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሰባሰቡ ውድ የታሪክ ቅርሶች ይገኙባታል።

በጎርጎራና አካባቢው እንዲሁም በጣና ሐይቅ ደሴቶች ውስጥ በርካታ ገዳማት ተገንብተዋል፡፡ ቁጥራቸው 44 ስለደረሰም “አርባ አራቱ ጎርጎራ” የሚል ስያሜ ወጥቶላቸው እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። ብዙዎቻችን “አርባ አራቱ ” የሚል ሀረግ ስንሰማ ቀድመን በዐይነ ህሊናችን የምናስበው ጎንደር ከተማ ነው፡፡

እርግጥ ነው፤ በጎንደር ከተማ አርባ አራቱ አድባራት እና ገዳማት ይገኛሉ። ከአርባ አራቱ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት መካከል አብዛኛዎቹ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ጠፍተዋል። የተወሰኑ ገዳማት ዘመን ቢሻገሩም ከተወሰኑ አሥርት ዓመታት በፊት ሀገራችን ባስተናገደቻቸው ተደጋጋሚ ጦርነቶች የተነሳ ወድመዋል።

አርባ አራቱ ጎርጎራ ተብለው ከሚጠሩት ውስጥ በ1312 ዓ.ም የተመሰረተችው የደብረሲና ማርያም አንድነት ገዳም አንዷ ናት። ገዳሟን የሠሯት የአፄ አምደ ጽዮን የጦር አዛዥ የሆነው ኤስድሮስ የሚባል ሰው ነው።
የጦር አዛዡ ኤስድሮስ በጎርጎራ አካባቢ የሚያስቸግሩ ሽፍቶችን በመደምሰስ ሕዝቡ በሰላም እንዲኖር ፣ ለሀገራቸው የሚጠበቅባቸውን እንዲገብሩ ካደረገ በኋላ ደብረሲና ማርያምን አሠርቷል።

ደብረሲና ማርያም በጣና ሀይቅ ዳርቻ የተመሰረተች በመኾኗ የጎንደር ነገስታት መዳረሻ እንደነበረች ይነገራል። ብዙ ነገስታቶችም ሃይማኖታዊ ተግባራትን ከመፈጸም በተጨማሪ በየጊዜው እድሳት ያደርጉላት ነበር። የአጼ ሱስንዮስ ልጅ የሆነችው መለኮታዊት ወደ ደብረ ሲና መጥታ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ትፈጽም እንደነበርም ታሪክ ያስረዳል፡፡

እቴጌ መለኮዊት በዚሁ ተጠምቃ ከበሽታዋ በመዳኗም “ለደብረሲና ምን ላድርግላት?” ብላ ሊቃውንቱን አማከረች። እነሱም “”ቤተክርስቲያኗ የግድግድ ስዕል የላትም፤ አሠሪላት” አሏት። ትእዛዙን በመቀበል በወቅቱ ጎጃም ውስጥ በስዕል ችሎታቸው የሚታወቁ ወንድማማቾችን በማነጋገር የግድግዳ ስዕሉን አሠራችች። ደብረሲና ማርያም በርካታ ለዕይታ የሚማርኩ ስዕሎች አሏት፡፡ የገዳሟ መስራች አባ ኤስድሮስ ከግብጽ እንዳመጧት በአፈ ታሪክ የሚነገርላት እና ምዕመናን “ግብጻዊት ማርያም” ሲሉ የሚጠሯት ስዕል በስተምሥራቅ በኩል ትገኛለች።

በሌላ በኩል ግብፃዊት ማርያምን እቴጌ መለኮታዊት በልዩ ሱባዔ እንዳሠራቻትና በአንድ ወቅት ተሰርቃ ወደ ግብፅ ተወስዳ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። ኾኖም ከሄደችበት ሀገር በታምር ወደ ደብረሲና ማርያም መመለሷ ይነገራል።
ግብፃዊት ማርያም የልቦና መሻትን የምትፈፅም እና ተዓምራትን የምታደርግ እንደኾነ የአካባቢው ምዕመናን ያምናሉ። አስገራሚው ነገር የግብፃዊት ማርያም ስዕል አሁን ድረስ ውበቷን እንደጠበቀች ትገኛለች።

የደብረሲና ማርያም የውስጥ የግድግዳ ላይ ሥዕሎቿ የተመራማሪዎችን ቀልብ ይስባሉ። ከ350 ዓመታት በላይ ያለ እድሳት የኖሩ ሥዕሎቿ ትናንትን ያሳያሉ፤ ጥንታዊ ታሪኩንም ይዘክራሉ።

ደብረሲና ማርያም አንድነት ገዳም ካሏት ዘመን ተሻጋሪ ቅርሶች መካከል በርካታ የብራና መጻሕፍት በግንባር ቀደምት ተጠቃሾች ናቸው።እነዚህን የብራና መጻሕፍት እና ሌሎች ቅርሶችን ለመታደግ አነስተኛ ቤተ- መዘክር አስገንብታለች፡፡ ከቅርሶች መካከል ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲያገለግሉ የነበሩ ተክሊሎች፣ ገድሎች፣ ድርሳናት፣ በገዳሟ ስም የተቀረፁ ማኅተሞች፣የብር መስቀሎች፣ ልብሰ ተክህኖዎች፣ ቃጭሎች፣ የጸበል ኩስኩሶችና መቋሚያዎች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።

በአማራ ክልል በሰሜናዊው የጣና ዳርቻ ጎርጎራ ላይ የምትገኘውን የደብረ ሲና ማርያም ገዳም ለመጎብኘት የሄደ ሁሉ ይህንን ታሪክ ይመለከታል።

አትሮንስ ዘተዋሕዶ ፣ሐመረ ኖኅ እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በድረ ገጾቻቸው ያወጧቸውን ጽሑፎች በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢንቨስትመንት ተቋማት ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ ነው” አቶ ደሳለኝ ጣሰው
Next articleየኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከቡሪኪና ፋሶ ጋር ያደርጋል።