“የኢንቨስትመንት ተቋማት ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ ነው” አቶ ደሳለኝ ጣሰው

62

ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2016 ዓ.ም (ዓ.ም) በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም እጦት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤የዜጎች ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ተገድቧል፡፡ በክልሉ ለወራት የቆዬው የሰላም እጦት በርካታ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ፈጥሮ አልፏል፡፡ በክልሉ አሁንም የተሟላ ሰላም ባይኖርም ከቀን ቀን የተሻለ ሰላም መኖሩ ተመላክቷል፡፡

በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት የኢንቨስትመንት ተቋማት ሥራቸውን ለማቋረጥ ተገድደውም ቆይተዋል፡፡

በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ እና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዲጅታል ሚዲያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በሃሳባቸውም በክልሉ በተፈጠረው ችግር በኢንቨስትመንት ዘርፉ በርካታ ችግሮች ማጋጠማቸውን አመላክተዋል፡፡ የሰላም እጦት የማያስቆመው ነገር አለመኖሩን የተናገሩት አቶ ደሳለኝ ኢንቨስትመንት፣ መልካም አሥተዳደር፣ ቱሪዝም እና ሌሎች ዘርፎች አስተማማኝ ሰላም እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

ከኢንቨስትመንት የሚገኝን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም አስተማማኝ ሰላም እና ጥሩ አሠራር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ ኢንቨስትመንት አሥተዳደራዊ ችግሮችን በፍጥነት የሚፈታ አሠራር እንደሚፈልግ ነው የጠቀሱት፡፡ የሚመጣውን ኢንቨስትመነት በሙሉ አቅም ለመጠቀም እና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ አስተማማኝ ሰላም፣ የሚሰብ የሥራ መስክ፣ የተሟላ መሠረተ ልማት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል፡፡

ሰላም በሌለበት ሁኔታ ኢንቨሰትመንት ሊታሰብ እንደማይችልም ተናግረዋል፡፡ ኢንቨስትመንት ሰላምን በእጅጉ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት አዲስ ኢንቨስትመንት እንዳይመጣ እና የነበሩትም ሥራ እንዲያቆሙ ምክንያት ሆኗል ይላሉ አቶ ደሳለኝ፡፡ ሥራ ማቆም ብቻ ሳይሆን የተዘረፉ እና የወደሙ የኢንቨስትመንት ተቋማት መኖራቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት የቱሪዝም እንቅስቃሴውም መቆሙን ነው የገለጹት፡፡

የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ለመታደግ እና ወደ ሥራ ለማስገባት ከፍተኛ ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ ቆመው የነበሩ የኢንቨስትመንት ተቋማት ወደ ሥራ እንዲገቡ እያደረግን ነውም ብለዋል፡፡ በሰላም እጦት ምክንያት ቆመው የነበሩ የልማት ፕሮጄክቶችም መልሰው እንዲጀምሩ እየተደረገ መኾኑን አመላክተዋል፡፡ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች እንዲመጡ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የአማራ ክልል ለሁሉም የኢንቨስትመንት አማራጮች የተመቸ ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ ምቹ ሁኔታዎችን ለመጠቀም በፍጥነት ወደ ሰላም መመለስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የሰላም ሁኔታውን በፍጥነት በማሻሻል ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን ለመከወን እየሠሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአውሮፓ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ምሽቱን ይካሄዳሉ፡፡
Next article44ቱ ጎርጎራ እና ደብረሲና ማርያም