
ባሕር ዳር: ኅዳር 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “አንድ ዕቅድ አንድ ሪፖርት” በሚል ርእስ ለምክር ቤት አባላት እና ለጽህፈት ቤቱ የሥራ ኀላፊዎች የተዘጋጀ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
ሥልጠናው ምክር ቤቱ ለሚያደርገው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ሚናው የጎላ መሆኑንም ነው የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶችን ዕቅድና ሪፖርት እንደሚመለከት እንዲሁም ስለተፈጻሚነታቸው በአካል ወርዶ በመስክ ምልከታ የሚያረጋግጥ መሆኑንም አፈ ጉባኤው አስታውሰዋል።
አፈ ጉባዔው “በዕቅድ መሰረት የተፈጸሙ ቁልፍ ሥራዎችን በአግባቡ መለየት ያስፈልጋል” ብለዋል። የክትትልና የቁጥጥር ሥራውን በውጤታማነት መንገድ ለመፈፀም የሚያስችል ሥርዓትም ሊኖር ይገባል ብለዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አስፋው የሀገሪቱን የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ምክር ቤቱ አጽድቆት ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመው፤ ይሁን እንጂ በየሴክተሩ የሚዘጋጁ ዕቅዶች ወጥነት የሌላቸው ከተቋም ተቋም የሚለያዩ እና ለክትትልና ለተጠያቂነትም ጭምር አስቸጋሪ እንደነበሩ አብራርተዋል።
ውጤታማ ሊያደርግ እና ተጠያቂነትን ሊያረጋግጥ የሚችል ዕቅድ ማዘጋጀት በማስፈለጉ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ “የአንድ ዕቅድ የአንድ ሪፖርት” የአሠራር ሥርዓት ተጀምሮ በ2015 ዓ.ም ትግበራ መጀመሩን አብራርተዋል። በቀጣይም በሁሉም ሴክተሮች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!