በአፍሪካ ብቸኛው ባለጥቁር ጋማ አንበሳ መገኛ ፓርክ!

119

ባሕር ዳር: ኅዳር 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል “አረንጓዴ መቀነት” እየተባሉ ከሚጠሩ ፓርኮች እና ጥብቅ ደኖች ውስጥ ቀዳሚው ነው። 2 ሺህ 666 ስኩየር ኪሎ ሜትር ወይም 266 ሺህ 570 ሄክታር ስፋት እንዳለው ይነገራል። ፓርኩ በሀገሪቱ ከሚገኙ 13 ብሔራዊ ፓርኮች በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፤ አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ።

ከ197ዐዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ‹‹ጥብቅ ደን›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፤ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ወደ ብሔራዊ ፓርክነት አድጓል፡፡

የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ኀላፊ ሙላው ሽፈራው እንዳሉት ፓርኩ 38 የአዕዋፍ፣ 52 የእንስሳት ዝርያዎችን እና 140 የሚኾኑ ተሳቢ እና ተራማጅ የእንስሳት ዝርያዎችን በውስጡ ይዟል። በኢትዮጵያ ከማገዶነት ያላለፉ፣ በመጥፋት ላይ የሚገኙ እና አዋጅ ወጥቶላቸው በልዩ ጥበቃ የሚገኙ እንደ ላሎ፣ ዞቢ፣ ግማርዳ፣ ወንበላ እና ሰርኪን የመሳሰሉ በርካታ የእጽዋት ዝርያዎችን በውስጡ ይዟል። ዝርያዎቹ ጎረቤት ሀገር ሱዳንን ጨምሮ በሌሎች ሀገራት ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ናቸው።

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በ2008 ዓ.ም ባካሄዱት ጥናት በአፍሪካ ብቸኛው ባለጥቁር ጋማ አንበሳ መገኛ ፓርክ መኾኑ ተረጋግጧል። በፓርኩ አጋዘን ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዝ ሲኾን ፌቆ፣ ሰሳ፣ ዝሆን እና ሌሎች የዱር እንስሳትም በሰፊው ይገኙበታል።

አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ከሱዳኑ የዲንደር ብሔራዊ ፓርክ ጋር በ70 ኪሎ ሜትር ይዋሰናል። መነሻውን ኢትዮጵያ ያደረገው የአይማ ወንዝ ከአልጣሽ ፓርክ በስተ ደቡብ ቤንሻንጉል ጉሙዝን እያካለለ በቀጥታ ወደ ሱዳኑ የዲንደር ፓርክ ውስጥ ይገባል። የገለጉ ወንዝ ደግሞ ከአልጣሽ በስተ ሰሜን ወደ ሱዳን ይፈስሳል። ሁለቱም ወንዞች ፓርኩን ድንበር አድርገው ነው ወደ ሱዳን የሚፈስሱት። በተለይም የሱዳኑ ዲንደር ፓርክ የአይማን ወንዝ ጨምሮ ሌሎች ወንዞች አቋርጠው የሚያልፉበት በመኾኑ ፓርኩ ዓመቱን ሙሉ ውኃ እንዲያገኝ አድርጎታል።

በአንጻሩ በአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ የሚፈስሱ አነስተኛ ወንዞች ለአደን ምቹ በመኾናቸው እና በበጋ ወራት ዘላቂ ባለመኾናቸው ዝሆንን ጨምሮ ሌሎች እንስሳት በበጋው ወራት ውኃ ለማግኘት ወደ ሱዳኑ የዲንደር ፓርክ ይሸሻሉ። በዚህም በበጋ ወቅት ወደ አልጣሽ ፓርክ የሚገቡ ጎብኝዎች እና ተመራማሪዎች እንስሳትን እንደማያገኙ ኀላፊው ነግረውናል። ይህንን ለማስቀረት ደግሞ የውኃ ገንዳ ማዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል። የአይማን ወንዝ 10 ኪሎ ሜትር በመቁረጥ ውኃው ወደ ፓርኩ እንዲገባ በማድረግ በበጋው ወራት ውኃ ፍለጋ የሚሸሹ እንስሳትን ማስቀረት እንደሚቻል አንስተዋል።

ከዚህ በፊት ለፓርኩ ስጋት የነበሩት የፈላታ ከብት አርቢዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት በተሠራው ሥራ ችግሩን መቅረፍ መቻሉን ነው ኀላፊው የገለጹት።

ይሁን እንጅ አሁንም ከቤንሻንጉል ጉሙዝ
ወደ ሱዳን ሚንቀሳቀሱ ሕገ ወጥ አዳኞች እና ኮንትሮባንዲስቶች ለእንስሳት ሥጋት ኾነዋል።

የካርበን ልቀትን በመከላከል ኢትዮጵያ እያበረከተች ለምትገኘው አስተዋፅኦ ትኩረት ባለመሰጠቱ ማግኘት የሚገባትን 75 በመቶ የካርቦን ሽያጭ እንድታጣ አድርጓታል። ፓርኩ ለክልሉ ብቻ ሳይኾን በረሃማነት ወደ ሀገሪቱ እንዳይስፋፋ እና ከሰሃራ በርሃ የሚነሳውን ጭጋግ መሰል አቧራ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ በመመከት ከፍተኛ ድርሻ ያለው መኾኑንም ገልጸዋል። በመኾኑም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለደን ልማት ትኩረት እንደተሰጠው ለፓርኩ ጥበቃም ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያን በሰው ሠራሽ አስተውሎት ከአፍሪካ ቀዳሚ የሚያደርጋትን ተቋም እውን መላድረግ እየሠራ መኾኑን የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
Next articleርእሰ መሥተዳድር ሙስጦፋ መሐመድ ኮምቦልቻ ከተማ ገቡ።