የበረሃዋ ገነት የኢትዮጵያን ልጆች ተቀብላ ለማስተናገድ ተሰናድታለች።

85

ጅግጅጋ: ኅዳር 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 18ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ “ብዝኀነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልእክት ይከበራል። የበረሃዋ ገነት ጅግጅጋ ከተማም ለበዓሉ ወደዚያው የሚያቀኑትን የኢትዮጵያዊ ልጆች ሁሉ ተቀብላ ለማስተናገድ ዝግጅቷን ስለማጠናቀቋ ከንቲባ ዚያድ አብዲ ተናግረዋል።

ከተማዋ በዓሉን ለሁለተኛ ጊዜ ነው የምታስተናግደው። የጅግጅጋ ከተማ ከንቲባ ዚያድ አብዲ ከተማዋ 1 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ የሚኖርባት እንደኾነች ገልጸዋል። ጅግጅጋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እድገት እያሳየች የመጣች ስለመኾኗም ከንቲባው ተናግረዋል።

ከተማዋ ካላት የሕዝብ ቁጥር አንጻር እያደገች የምትሄድ በመሆኗ ቀድሞ ከነበረው 6ሺ ሄክታር አሁን ወደ 11ሺ ሄክታር የቆዳ ስፋት ከፍ ማለቷን ጠቁመዋል። በመሰረተ ልማት ግንባታ ሽፋንም ከፍተኛ ለውጥ አለ ነው ያሉት። ከ5 ዓመታት በፊት 14 ኪ.ሜ የአስፋልት መንገድ የነበራት ሲኾን አሁን ላይ 44 ኪ.ሜ መድረስ መቻሉን ከንቲባው ተናግረዋል። የአረንጓዴ ልማትና የከተማ ውበት ሥራዎችም በትኩረት እየተሠሩ ስለመኾኑ አስገንዝበዋል።

በኢንቨስትመንት ፍስሰት በኩልም የተሻለ እንቅስቃሴ እየታዬ ነው። ከንቲባው እንደገለጹት በርካታ ዲያስፖራዎች ወደ ከተማዋ እየተመለሱ ኢንቨስት እያደረጊ ነው።

በበርበራ እና ጅቡቲ ወደብ አቅራቢያ መሆኗ እያሳየች ካለችው የቢዝነስ እንቅስቃሴ ጋር ተደማምሮ ከተማዋ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ወደፊት የንግድና ኢንቨስትመንት ማዕከል ለመኾን ያስችላታል፤ ለዚህም በትኩረት እየሠራን ነው ብለዋል ከንቲባው።

ታሪካዊው ድል የተመዘገበበት የካራማራ ተራራ በከተማዋ ቅርብ ርቀት መገኘቱም ጅግጅጋን ለጎብኝዎች መዳረሻ እንደሚያደርጋት ተናግረዋል።

“ሕዝቡ እንግዶቹን ለመቀበል ዝግጁ ነው፤ ጅግጅጋ የሁሉም ብሔረሰቦች ከተማ ናት፤ አንድ ላይ ይነግዳሉ፤ ይሰራሉ፤ አብረውም ይኖራሉ” በማለት አብሮነቱን አንስተዋል።

“የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች ወደ ከተማችሁ በሰላም ኑ” ሲሉም ጋብዘዋል። አስተማማኝ ሰላም ባለባት ጅግጅጋ 30 የሚደርሱ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ተገንብተው ለእንግዶች ዝግጁ ናቸው ብለዋል።

ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግሥቴ – ከጅግጅጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችን በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት እየተሠራ ነው” አቶ መለሰ ዓለሙ
Next article“ስለ ጎንደር ሰላም የሰማነው እና ተገኝተን ያረጋገጥነው ፈጽሞ አይገናኝም” ሠልጣኝ የመንግሥት አመራሮች