
ባሕር ዳር: ኅዳር 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 3ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ሥልጠና በተለያዩ ከተሞች እየተሰጠ ይገኛል። ሥልጠናው በባሕር ዳር ከተማም እየተሰጠ ነው።
በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መለሰ ዓለሙ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለተውጣጡ የሥራ ኀላፊዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ እና በጋራ ሥልጠና እንዲሰጥ መደረጉ የሥራ ኀላፊዎችን የመፈጸም አቅም እና የእርስ በእርስ ትውውቅ ያጎለብታል ብለዋል። የማኅበረሰቡን ወግ እና ባሕል ለማስተዋወቅና ለማጠናከርም ፋይዳው የጎላ መኾኑን ተናግረዋል። ከዚህም ባለፈ የተጀመሩ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን ለማጠናከር አጋዥ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ኅላፊው በአማራ ክልል የተፈጠረውን የሰላም ችግር ለመፍታት መንግሥት ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። የሚነሱ የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር እና ሌሎች ጥያቄዎችን በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የሁሉም ሕዝቦች ጥያቄ፣ የሌሎች ሕዝቦች ጥያቄዎችም የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ነው ሲሉም ተናግረዋል። ጥያቄዎች ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን በተከተለ መልኩ እንዲመለሱ መንግሥት እየተሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል።
መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጥ ያነሱት አቶ መለሰ ለዚህም ከሀገር ውስጥ ባለፈ ከጎረቤት ሀገራት ጋርም በሰላም ችግሮችን እየፈታ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም ደግሞ የውስጥ ችግሮችን በሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶችን ጭምር እየፈታ ይገኛል ብለዋል።
የግጭት የመጨረሻ ውጤቱ ጥፋት መኾኑን ያነሱት አቶ መለሰ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ሁሉም ወገን ለሰላም ዘብ እንዲቆም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!