
ባሕር ዳር: ኅዳር 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከመላው ኢትዮጵያ ተሰባስበው ለ3ኛ ዙር በባሕር ዳር የሚሠለጥኑ የመንግሥት አመራሮች የባሕር ዳር ከተማን የኢንቨስትመንትና የልማት ሥራዎች ጎብኝተዋል።
ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ የመጡት አባስ አሕመድ የባሕር ዳር ቆይታችን የሚመችና ትምህርት ያገኘንበት ነው ብለዋል። ከተማዋ ወደ ጥሩ የልማት መስመር መግባቷን እና የኢንዱስትሪ ከተማ ኾና እንዳገኟት ገልጸዋል። ከአውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ እስከ ሥልጠና ቦታ ድረስ የተደረገልን አቀባበልና የሕዝቡ ጨዋነት የሚመሰገን ነውም ብለዋል።
ሌላዋ ጎብኚ ወይዘሮ ከበቡሽ ተካበ በጎበኙዋቸው የልማት ሥራዎች መደሰታቸውንና ልምዱን ለክልላቸው እንደሚወስዱ ገልጸዋል።
ከደቡብ ኢትዮጵያ የመጡት አቶ ተካልኝ በየነ በጉብኝታቸው አበረታች ልማት መኖሩን አይተናል፤ ባሕር ዳር በጥሩ የልማት መስመር ላይ ናት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ልማት መኖሩ ደስ ይላልም ብለዋል። ወደ ባሕርዳር ጉዞ ስንጀምር የሰማነው የከፋ ችግር እንዳለ ነበር፤ በቦታው ተገኝተን ስናየው ግን አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ነው ያየነው ሲሉም አክለዋል።
ከሥልጠናው እና ጉብኝቱ ባገኘነው ግንዛቤ ልማትን ወደ ክልላችን እናሰፋለን ያሉት አቶ ተካልኝ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በአንድ ላይ ስለ ኢትዮጵያ የመምከር ጅምራችንን ወደ ሕዝቡም እናሰርጻለን ብለዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ