“የዘመኑ ራስ ምታት፤ የኑሮ ውድነት”

166

ባሕር ዳር: ኅዳር 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ሳይነሳ የዋለበት ቀን የለም፡፡ ታላላቆቹ ያነሱታል፤ ታናናሾቹም ያወሱታል፤  እናት የልጆቿን ዓይን ለማየት እስከመሳቀቅ ደርሳለች፤ ምግብ ስጡኝ የሚሉት ልጆቿን ለማጉረስ፣ በረደኝ አልብሱኝ የሚሏትን ለማልበስ ተሳቃለች፡፡ የኑሮ ውድነት ከፊት እና ከኋላዋ ፤ ከግራ እና ከቀኟ ጠፍሮ ይዟታልና፡፡

ቸር አውለኝ ከማለቱ አስከትሎ ምን እበላ ይሆን ብሎ የሚያስበው ብዙ ነው፡፡ ቸር አሳድረኝ ብሎ በሰላም ከሚተኛው ለነገ ስለሚበላው፣ ልጆቹንም ስለሚያበላው ሲጨነቅ ፣ ሲጠበብ፣ ሲብሰለሰል የሚያድረው የትየለሌ ነው፡፡

የዘመኑ ራስ ምታት ነው፤ የኢትዮጵያውያንን ጓዳ አንኳኩቷል፡፡ ኢትዮጵያውያን በቀን ከሚያገኙት ገቢ ይልቅ በቀን የሚያወጡት ወጪ በርክቶባቸው ተቸግረዋል፡፡ “በእንቅርት ላይ ጀሮ ደገፍ” እንዲሉ ከሰላም እጦት በተጨማሪ የኑሮ ውድነት ለኢትዮጵያውያን ፈተና ኾኗል፡፡ በሰላም እጦት የሚቸገሩት ኢትዮጵያውያን የኑሮ ውድነት ሕይወታቸውን አክብዶባቸዋል፡፡  

ከሰሞኑ መደበኛ ስብሰባው ባደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  መንግሥት ኢትዮጵያውያንን ከኑሮ ፈተና ለመታደግ ምን እየሠራ እንደሆነ ተጠይቆ ነበር፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ  በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ሁለት አንገብጋቢ ጥያቄዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡ ሰላም እና የኑሮ ውድነት፡፡ የሰላም እጦት የኑሮ ውድነቱን ያባብሳል፡፡ የኑሮ ውድነት መናር ደግሞ ሰላም እንዳይኖር ይቆሰቁሳልና፡፡ዛሬ የሚጎርሰው የሌለው እና ለነገ እንደማይበላ ያወቀ ሁሉ ጉርስ ለማግኘት የሚያስችለውን የትኛውንም አማራጭ ይወስዳልና ሰላም ያን ጊዜ  አደጋ ውስጥ ትገባለች፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰላም እጦት ምርት ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ ኢትዮጵያውያንን ለችግር እንደዳረጋቸው በምክር ቤት አባላቱ የተነሳ ጉዳይ ነው፡፡ የምርት አለመቅረብ የኑሮ ውድነቱን ጣሪያ ሰቅሎታል ነው ያሉት፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የሰላም እጦት ባለበት አካባቢ አርሶ አደሮች ተረጋግተው ምርት ማምረት ባለመቻላቸው ችግሩን እንዲባባስ አድርጎታል፡፡ የሰላም ሁኔታው በአጭር ጊዜ ካልተስተካከለ የኑሮ ውድነቱ አሁን ካለበት ሊብስ ይችላልም ብለዋል፡፡ 

የኑሮ ውድነቱ ዜጎች ሳይወዱ በግድ ጎዳና እንዲወጡ እያስገደዳቸው ነው፤ ቤት አልባ አድርጎ የሰው እጅ እያሳያቸው ነው፤ የኢትዮጵያውያን አኗኗር እጅግ ተለያይቷል፤ የዜጎች እንቅስቃሴ ተገድቧል፤ ሠርቶ መብላት አደጋ ውስጥ ገብቷል ነው ያሉት የምክር ቤት አባላቱ፡፡ መንግሥትስ ሀገር እና ሕዝብን እንዴት ሊታደግ አስቧል ሲሉም ጠይቀዋል፡፡


የውጭ ምንዛሬ መጨመር ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ተጽዕኖ እንዳለው ያነሱት አባላቱ በውጭ ምንዛሬው ጭማሬ ሰበብ ግን ብዙዎች ያለ አግባብ ዋጋ ጭማሪ በማድረግ የዜጎችን ሕይወት አክብደውታልም ብለዋል፡፡

ከምክር ቤት አባላቱ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር)  ኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት እድገቷ ከፍ እያለ ቢሄድም በየቤቱ ያላውን ችግር ግን መፍታት አልቻለም ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር እና ድህነት በቀላሉ የሚፋቅ አለመኾኑንም አብራርተዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ ስር የሰደደውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል መሠረት መጣል ግን በዚህ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡

ያለውን የችግር እና የድህነት ጥልቀት በወጉ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ረጅም እና አታካች ሥራዎችም ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡ በግብርና የተጀመረውን ውጤታማ ሥራ ማስቀጠል ችግሩን ለመፍታት አንደኛው መንገድ እንደኸነም አንስተዋል፡፡ ምርት እና ምርታማነትን መጨመር ምጣኔ ሃብትን ለማሳደግ እንደሚረዳም ገልጸዋል፡፡ የወጪ የእዳ ክፍያ መጨመር የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲገጥም እንዳደረገውም አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ኑሮ ውድነቱ ሲናገሩ “ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች በኑሮ ውድነት ምክንያት ለመመገብ ይቸገራሉ፤ ከእኛ ቢሮ በመቶ ሜትር ሰዎች ይቸገራሉ፤ ሩቅ መሄድ አያስፈልጋችሁም፤ በዓለም ላይ ባለፉት አርባ ዓመታት ያልታዬ  የዋጋ ግሽበት አለ፡፡ የኢትዮጵያ ችግር ብቻ ሳይኾን የዓለም ችግር ነው፤ የኢትዮጵያን ያባባሰው የዋጋ ግሽበቱ የገቢ አቅማችን ዝቅተኛ በኸነበት ኹኔታ መፈጠሩ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሳይቋረጥ መምጣቱ ነው” ብለዋል፡፡ 

የሰው የገቢ ምጣኔ እና የዋጋ ግሽበት አለመመጣጠን በአኗኗር ላይ ጫና አምጥቷል፤ የሚካድ ነገር አይደለም ነው ያሉት፡፡ የዓለም የዋጋ ተመን ምጣኔ እንደሚቀንሱ ትንቢያዎች እንዳሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያም ዋጋ ተመን እየቀነሰ መኸኑን ነው የተናገሩት፡፡

“ፈተናን አናስቀረውም፤ ፈተናን አንፈልግህም እና  አትምጣብን አንለውም፤ ነገር ግን ፈተና ሁልጊዜ መልኩ ስለሚለያይ መልኩ የሚለያዬውን ፈተና እንደ አግባቡ ተገንዝቦ መወጣት ብቻ ነው መፍትሔው ” ብለዋል ።አሁን ያለውን ችግር እንዴት መፍታት ይቻላል የሚለውን ሲያብራሩ ለዘመኑ ራስን ማዘጋጀት እንጂ ፈተና አልቦ ጉዞ  አለመኖሩንም አመላክተዋል፡፡ እንፈተናለን ለፈተናው ራሳችን እያዘጋጀን እያሸነፍን መሄድ አለብን ነው ያሉት፡፡

መንግሥት እየወሰደ ስላለው መፍትሔ ሲናገሩም እጅ አጠር ዜጎች እንዳይጎዱ በኢኮኖሚ የሚንቀሳቀሰውን ሃብት ለመያዝ ሞከረናል፤  ምርታማነትን ማሳደግ ላይ በትኩረት ሠርተናል ብለዋል፡፡ መንግሥት ድጎማ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡ የእሁድ ገበያ መስፋፋትም የኑሮ ውድነትን ለመዋጋት የተወሰደ እርምጃ ነው ብለዋል ፡፡

የቤት ኪራይ ዋጋ በየቀኑ እየጨመረ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጫና አምጥቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቤት ኪራይ ጋር በተያያዘ የሚነሳው ችግር በቅርቡ መፍትሔ ሊያገኝ እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡ ዋጋ እንዲረጋጋ መንግሥት በርካታ ምርቶችን እንደሚያስገባም ገልጸዋል፡፡ በኑሮ ውድነት ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች እና  ውጤቶችን ማስቀጠል፣ ምርታማነትን ማሳደግ፣ ሕዛባችን ያለበትን መከራ ደረጃ በደረጃ መቀነስ አለብንም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚቀጥሉት ዓመታት ከእንደዚህ አይነት ቋንቋዎች ሊወጣ እንደማይችል ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት ያነሱት የዶላር እጥረት፣ ኑሮ ውድነት ፈተና እና በምርታማነት ላይ የሚነሳው ጥያቄ  ነው ብለዋል፡፡ ተረባርበን ልጆቻችን ይሄን ጥያቄ እንዳይጠይቁ እንሥራ እንጂ በቀላሉ የሚፈታ አድርገን አናስበው ነው ያሉት፡፡  ምርትእና  ምርታመነትን ለማሰደግ  እተሠሩ ያሉ ሥራዎች ሌሎች የመፍትሔ እርምጃዎች ለውጥ እና እድገት ግን የሚጨበጥ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

በደብረ ታቦር ዪኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ  መምህር ኃይሌ አደመ (ዶ.ር) የዋጋ ግሽበት ለኑሮ ውድነት መፈጠር አንደኛው ምክንያት ነው ይላሉ፡፡
ፍላጎት እየላቀ ሄዶ የምርት እጥረት ሲኖር ለኑሮ ውድነት መባባስ ሌላኛው ምክንያት መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የተዛባ የገንዘብ ፖሊሲ ግሽበት እንዲኖር ያደርጋል፤ ግሽበት ደግሞ የኑሮ ውድነትን ያባብሰዋል ነው ያሉት፡፡
የመዋቅራዊ  ችግሮችም የዋጋ ግሽበት እንደሚያመጡም ተናግረዋል፡፡ የሃብት እጥረት በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች ሊከሰት  እንደሚችል ያነሱት መምህሩ ለአብነት በዝናብ እጥረት ምክንያት ድርቅ ሲከሰት የምርት እጥረት ይከሳታል ነው ያሉት፡፡ ያልተገባ ትርፍት ለማግኘት ሲባል ምርትን መደበቅ፣ ምርቶች ከቦታ ቦታ እንዳይነቀሳቀሱ ማድረግ የምርት እጥረት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ሰው ሠራሽ ምክንያቶች መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡  የሰላም እጦት ንብረት በአግባቡ እንዳይነቀሳቀስ እንደሚያደርገው እና ዜጎችን ለኑሮ ውድነት እና ለሌሎች ችግሮች እንደሚያጋልጣቸውም ገልጸዋል፡፡

ምጣኔ ሃብት በፖሊሲ ሳይኾን በደላሎች ሲመራም ችግሩንን ያባብሳል ይላሉ አቶ ዶክተር ሀይሌ።ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ችግርም ምርት በደላሎች መመራቱ ነው ብለዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ዋነኛ ተግባር ዋጋን ማረጋጋት መኾን እንደሚገባውም ገልጸዋል፡፡ የዋጋ ግሽበት ሲኖር ገንዘብ የመግዛት አቅም እያሽቆለቆለ ይሄዳልም ብለዋል፡፡ የዋጋ ግሽበት በየጊዜው መጨመር እና ገንዘብ የመግዛት አቅሙ ማሽቆልቆል ቋሚ ገቢ ያላቸውን ዜጎች በእጅጉ እንደሚጎዳም አመላክተዋል፡፡ ቋሚ ገቢ ያላቸው ዜጎች የዋጋ ግሽበት በጨመረ ቁጥር መሠረታዊ ፍጆታዎችን ሟሟላት ወደ ማይችሉበት ደረጃ ይደርሳሉም ብለዋል፡፡

የኑሮ ውድነት እየከበደ፣ ዜጎች መብላት እየተቸገሩ በሄዱ ቁጥር ከማማረር አልፈው  ወደሌላ አቅጣጫ እንዲሄዱ ያስገድዳቸዋል ነው ያሉት፡፡ የዋጋ ግሽበት እየጨመረ ሲሄድ ቁጣባ በእጅጉ ይጎዳል ያሉት ምሁሩ ቁጠባ ከሌለ ኢንቨስትመንት አይኖርም፤ ኢንቨስትመንት ከሌለ የሥራ አጥነት ቁጥር ይጨምራል፤ የሥራ አጥነት ቁጥር ሲጨምር ደግሞ ሌላ ችግር ይፈጠራል ብለዋል፡፡

የዋጋ ግሽበት እንደ ቀላል እንደማይታይ ያነሱት ምሁሩ ችግሮችን ለመፍታት ብሔራዊ ባንክ የተረጋጋ ዋጋ እንዲኖር ማድረግ እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡ የኑሮ ውድነትን ለመዋጋት መፍትሔዎችን ሲያመላክቱም መንግሥት የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ መዋቅራዊ ችግሮችን መቅረፍ ይገባዋል ብለዋል፡፡ የሰላሙን ጉዳይ ማስተካከል ሌላኛው መፍትሔ መኾኑን ያመላከቱት ምሁሩ ግብዓት ከቦታ ቦታ የማይንቀሳቀስ፣ ምርት እያለ የማይቀርብ ከኾነ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል ብለዋል፡፡ በአጭር ጊዜ መፍታት የሚገባውን መፍታት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡

ሰላም የሚመጣባቸውን መንገዶች በአጭር ጊዜ አሟጦ መጠቀም እና የኑሮ ጫናን ማቀለል የተገባ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ መዋቅራዊ ችግሮችን በአስቸኳይ መፍታት እና  ሰላምን ማረጋገጥ የኑሮ ውድነቱን ክብደት ለመቀነስ የአጭር ጊዜ መፍትሔዎች መኾናቸውን አንስተዋል፡፡

በዘላቂነት ችግሮችን ለመፍታት ደግሞ ምርት እና  ማርታመነትን መጨመር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ፍላጎትን ሊያረካ የሚችል ምርት እና ምርታመነትን መጨመር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ ምርትን በግብርና ብቻ ሳይኾን በሁሉም ዘርፍ መጨመር ይገባልም ብለዋል፡፡ ምርትን መጨመር ብቻ መፍትሔ አይኾንም ያሉት ምሁሩ ምርትን በአግባቡ መጠቀም እና መዋቅራዊ ችግሮችን መፍታት አስፈላጊ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበፓሪስ ኦሎምፒክ ለሚሳተፈው የኢትዮጽያ አትሌቲክስ ቡድን የመለማመጃ ስታዲየም ፈቃድ ስምምነት ተደረገ።
Next article“ባሕር ዳር በጥሩ የልማት መስመር ላይ ናት” ሠልጣኝ የመንግሥት አመራሮች