“ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሀገር ገጽታን ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው” አምባሳደር መሥፍን ቸርነት።

59

ባሕር ዳር: ኅዳር 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከተጀመረ ሃያ ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረው ታላቁ ሩጫ ነገ ይካሄዳል። ከተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች እና ከአስር ሀገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች ይካፈሉበታል ተብሎም ይጠበቃል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ ውድድሩ በሁሉም ሰው ተወዳጅ እና ተናፋቂ እንዲኾን እየሠራን ነው ብለዋል። በዘንድሮው መርሐ ግብርም 45 ሺህ ሰዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ የመወዳደሪያ ቲሸርቶች ተሽጠዋል ብለዋል።

የታላቁ ሩጫ መስራች አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካን የመሳሰሉ ሀገራት ትልልቅ ውድድሮችን በመዘጋጀት አፍሪካን አኩርተዋል ብሏል።

ኢትዮጵያም ይህን ማድረግ ትችላለች፤ ብዙ ፍይዳም ያስገኛል ሲል ገልጿል።

የባሕል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባሕል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መሥፍን ቸርነት ውድድሩ ቱሪዝምን እና ዲፕሎማሲን ከማጠናከር ባለፈ የሀገርን ገጽታ ይገነባል ብለዋል።

የዘንድሮው ውድድር የክብር እንግዶች የዓለም ግማሽ ማራቶን አሸናፊ ኢሊያና ሜየር እና እውቁ የሩጫ የቀጥታ አስተላላፊ ቲም ሃቺንግስ ናቸው።

ታላቁ ሩጫ በተሳታፊዎች ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ሲኾን ከዓለም ምርጥ አስር የጎዳና ላይ ሩጫዎች ውስጥ እንደሚካትም የኢቢሲ ዘገባ ያሳያል።

ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያውያን ተከባብረን እና ተዋደን ስንኖር ሰላም እና ልማት ይመጣል” የጎዴ እና ቀብሪ ደሃር ከተማ ነዋሪዎች
Next articleየአውሮፓ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ፡፡