አቢሲንያ ባንክ አጠቃላይ የተቀማጭ የገንዘብ መጠኑን 158 ነጥብ 53 ቢሊዮን ብር ማድረሱን ገለጸ።

52

አዲስ አበባ: ኅዳር 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አቢሲንያ ባንክ አጠቃላይ የተቀማጭ የገንዘብ መጠኑን 158 ነጥብ 53 ቢሊዮን ብር ማድረሱን ገልጿል። ባንኩ የባለአክሲዮኖች 27ኛ መደበኛ እና 14ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔዎች አያካሄደ ይገኛል። አቢሲንያ ባንክ ከቀዳሚ የግል ባንኮች መካከል አንዱ በመኾን ባለፉት 27 ዓመታት ሁሉን አቀፍ ዕድገት ማስመዝገቡ በመድረኩ ተገልጿል።

ባንኩ የካቲት 1988 ዓ.ም በ18 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ከግል ባንኮች መካከል አንዱ በመኾን ወደ ሥራ ገብቷል። ሰኔ/2015 ዓ.ም በነበረው የሒሳብ መግለጫ መሰረት የባንኩ አጠቃላይ ሒሳብ 189 ነጥብ 51 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል።

የብድርና ቅድመ ክፍያዎች መጠን 146 ነጥብ 51 ቢሊዮን ብር መድረስ እንደቻለም ነው በስብሰባው የተብራራው። በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻም የባንኩ ጠቅላላ ገቢ 22 ነጥብ 73 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲኾን በዓመቱ የተመዘገበው ጠቅላላ ወጪ 17 ነጥብ 50 ቢሊዮን ብር ተቀንሶ 5 ነጥብ 23 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አስመዝግበዋል።

በተለይም ባንኩ የ5 ዓመት መሪ ዕቅዱን ተግባራዊ በማድረግ ለሁሉም ኅብረተሰብ ተደራሽ ለመኾን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በሠራው ሥራ ከፍተኛ ሀብት መሰብሰብ ችሏል።

ባንኩ ተግባራዊ ባደረገው የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ አቅጣጫ መሠረት የ45 ነጥብ 5 በመቶ ዓመታዊ የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት እና የ44 ነጥብ 5 በመቶ ዓመታዊ የሀብት ዕድገት አስመዝግቧል።

በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ አዳዲስ የለውጥ እርምጃዎችን ተከትሎ የባንክ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባለሀብቶች መፍቀዱ የሚፈጥረውን ተጨማሪ ውድድር ለመቋቋም የሀገር ውስጥ ባንኮች በቂ የካፒታል አቅም ሊይዙ እንደሚገባም ተነስቷል።

ዘጋቢ፦ ወንድም ደባሽ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኃያላን ሀገራት ከዛሬ ደረጃቸው የደረሱት እርስ በእርስ ተጋጭተው ሳይኾን ችግሮቻቸውን ተመካክረው በማለፍ ነው” የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማኅበር ተወካይ ካፒቴን ሰለሞን ግዛው
Next article“የተሻለ ሰላም በመኖሩ የልማት ሥራዎችን እየሠራን ነው” የቀብሪደሃር ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር አብዱረዛቅ አወል