
አዲስ አበባ: ኅዳር 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ሚና እና ተሳትፎ ለሀገራዊ ምክክር እና ለሀገራዊ መግባባት በሚል ከዲያስፖራ ማኅበረሰቡ ጋር በአዲስ አበባ ውይይት እየተካሄደ ነው።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የዴሞክራሲ ብዙ ልምድ ባለበት የኖራችሁ እና ሀሳብ የምታካፍሉን ኢትዮጵያውያን ወገኖች በቂ ሀሳብ አንደምታካፍሉን እናምናለን ሲሉ ተናግረዋል።
በተለያዩ ሀገራት ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎችን የምትወክሉ ወገኖቻችን ከእናንተ የምንጠብቃቸው ብዙ ሀሳቦች ብዙ ነገሮች አሉ፤ እናንተ ዘርፈ ብዙ ተባባሪዎቻችን ሆናችሁ ሀሳብ እና ልምድ አንድታካፍሉን እጠይቃለሁ ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዲያስፖራ ማኅበር የቦርድ አባል እና የአዲስ አበባ ተወካይ ካፒቴን ሰለሞን ግዛው እንዳሉት ይህ ፕሮግራም የተዘጋጀው በየትኛውም ሁኔታ ከሀገሩ ጎን የሚቆመው ዲያስፖራ ማኅበረሰብ ሀሳቡን አንዲያካፍል ለማስቻል ነው ብለዋል። “ኃያላን ሀገራት ከዛሬ ደረጃቸው የደረሱት እርስ በእርስ ተጋጭተው ሳይኾን ችግሮቻቸውን ተመካክረው በማለፍ ነው”ሲሉም ተናግረዋል።
ባለጉልበት እና በለሀብት ሆነው የምንመለከታቸው ሀገራት ሁሉ ከመገፋፋት መመካከርን፣ ከመለያየት አንድ መሆንን እና መነጋገር ስለመረጡ ነው ዛሬ የተረጋጉ ኃያል የሆኑት ብለዋል። ኢትዮጵያ ታፍራ እና ተክብራ አንድትኖር ዜጎቿ ይህንን ማድረግ እና መመካከር ይኖርባቸዋል ሲሉም መክረዋል።
ወደራሳችን ተመልሰን ችግሮቻችን ከፈታን፣ የምንመለከታቸው ችግሮች እና የአንድነት ቀዳዳዎች በውይይትና በምክከር ከቀረፍን፣ ሀገራችን በቱሪዝም ሀብት ብቻ ያሏት አቅሞች ለታላቅነቷ ምንጮች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አንዷለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!