
እንጅባራ: ኅዳር 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በርካታ ወንዞች እና ሐይቆች ይገኛሉ። ለአብነት አዩ፣ ድራ፣ አጣም፣ ዲም፣ ግዛኒ የተባሉ እና ሌሎች ወንዞች ባለቤት ነው፡፡ ትስኪ፣ ፋንግ፣ ጋርች የተሰኙ ፏፏቴዎች እንዲሁም ዚምቢሪ እና ጥርባ የሚባሉ ሐይቆች ይገኙበታል። ዘንገና ሐይቅ ደግሞ ዋነኛው ነው።
የሐይቁ መገኛ በባንጃ ወረዳ በከሳ ቸውሳ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ ከእንጅባራ ከተማ በስድስት ኪሎ ሜትር ርቅት በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ ይገኛል፡፡ ከአዲስ አበባ በ430 ኪሎ ሜትር፣ ከባሕር ዳር ደግሞ በ127 ኪሎ ሜትር ይርቃል፡፡
የዘንገና ሐይቅ የእንቁላል ቅርጽ አለው፡፡ አጠቃላይ ሥፋቱ 55 ሄክታር ነው ፤ ከባሕር ጠለል በላይ 2 ሺህ 515 ሜትር ከፍታም አለው።
ወደ ሐይቁ በእግር መሔድ የሚፈልጉ ጎብኚዎች በጫካው መሀል ዘና-ፈታ እያሉ እና ንጹህ አየር እየሳቡ መጓዝ ይችላሉ።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባወጣው ጥናት መሰረት ሐይቁ 150 ሜትር ጥልቀት አለው፡፡ ርዝመቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ አንድ ኪሎ ሜትር ተለክቷል፡፡ የእንቁላል ቅርጽ ያለው የዘንገና ሐይቅ በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ መፈጠሩን ተመራማሪዎች ያስረዳሉ፡፡
የሐይቁ ውኃ ያረፈው ሰው በራሱ እጅ እንደሰራው ገበቴ ተፈጥሮ ባዘጋጀው ስፍራ ነው፡፡ ውኃውን ከምድር ኾነው ሲያዩት እንደ መስታወት ያንጸባርቃል፡፡ ፀጥ ረጭ ያለ ነው፡፡ አየር ላይ ኹነው ሲመለከቱት አረንጓዴ፣ መሬት ላይ ሲያዩት ደግሞ ሰማያዊ ቀለም አለው – ኅብር በሉታ!
የሐይቁ ቀለም አረንጓዴ እና ሰማያዊ የኾነው በዙሪያው ባሉት እፅዋት ነጸብራቅ ምክንያት እንደኾነ ይታመናል፡፡
በተለያዩ እጽዋት የተከበበ ነው፡፡ ከ75 በላይ የእፅዋት ዝርያዎች፣ የዱር እንስሳት እና አእዋፋትም በዙሪያ ገባው እንደሚገኙም ከባንጃ ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ ለምሳሌ ጦጣዎች፣ የዱር ቀበሮዎች፣ ጅቦች፣ አሳማዎች፣ አጋዘኖች፣ ቀበሮዎች ወዘተ በሐይቁ ዙሪያ በሚገኙ እፅዋት ውስጥ በብዛት ይገኛሉ፡፡
ዳክዬ፣ ቁራ፣ ጭልፊት፣ ርግብ፣ ጉጉትና ሌሎች የአእዋፍ ዝርያዎችም ዘንገና ሐይቅ መኖሪያቸው ነው።
ዘንገና ባለብዙ ጸጋ ነው። እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ፣ አስተማማኝ ሰላም፣ ተስማሚ የአየር ጸባይ እና መሰል ምቹ ሁኔታዎችን የታደለ ነው፡፡ በመኾኑም ይህን ውብ የተፈጥሮ ጸጋ የውጭ ሀገራት ዜጎች እና በሺህዎች የሚቆጠሩ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች በመጎብኘት አብዝተው አትርፈውበታል፡፡
የዘንገና ሐይቅን የተሻለ የጎብኝዎች መዳረሻ ለማድረግ በዙሪያው የእንግዳ ማረፊያዎች ግንባታ እየተከናወነ ነው፡፡ ሐይቁ እምብዛም ያልተጎበኘ እና ያልተጠቀምንበት ግን ማራኪ ሃብታችን ነው፡፡ በሐይቁ ውስጥ ቦርፊሽ ፣ ቲላፒያና ባርቤል የተባሉ የዓሣ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰፊ የደን ሃብት፣ ትልልቅ ዋሻዎች፣ ገዳማት እና መሰል ታሪካዊ እንዲኹም ተፈጥሮአዊ የመስህብ ሃብቶች የታደለ ነው፡፡ በመኾኑም ወደዚያ ያቀና ሁሉ ተዝናንቶ፤ በማኅበረሰቡ የእንግዳ ተቀባይነት እሴት ተደንቆ ይመለሳል።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!