
ባሕር ዳር: ኅዳር 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የመጽሐፍት ስርጭትን በትኩረት እንዲያከናውን በክልሉ ምክር ቤት የሰው ሃብት እና የቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሜቴ አሳስቧል።
ቢሮው የ2016 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን በቋሚ ኮሚቴው አስገምግሟል።
በግምገማው ትምህርት ቢሮው ለ2016 የትምህርት ዘመን ያደረገው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እና በበጀት ዓመቱ 1ኛ ሩብ ዓመት ያከናወናቸው ሥራዎች ቀርበዋል፡፡
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የትምህርት መሣሪያዎችን ለማዳረስ በትኩረት ተሠርቷል ብለዋል። የጸጥታ ችግር ቢኖርም የተሻለ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ትምህርት ለማስጀመር የተሠራው ሥራ አበረታች እንደኾነም በውይይቱ ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ቤት ምገባ እና አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ለማጠናከር የተሠሩ ሥራዎች መልካም ጅማሮዎች መኾናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
የትምህርት ቤቶች ደረጃ ዝቅተኛ መኾን እና የ12ኛ ክፍል ውጤት ማሽቆልቆል በቀጣይ በትኩረት ተይዘው ሊሠራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ኾነው በምክር ቤቲ ተነስተዋል።
በአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሀብት እና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት አበራሽ ታደሰ በተደረገው ግምገማ ትምህርት ቢሮው የጸጥታ ችግሩ በሚስተካከልባቸው አካባቢዎችን በመከታተል ትምህርት እንዲያስጀምር፣ የመጽሐፍት ስርጭት ችግርን በፍጥነት እንዲቀረፍ እና አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በተዘጋጀው መጽሐፍ እንዲጀመር ተወያይተናል ብለዋል፡፡
ወይዘሮ አበራሽ ከደረጃ በታች የኾኑ ትምህርት ቤቶች ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሻሻሉ እና በትምህርት ጥራት ላይ ተጠያቂነት እንዲኖር ቋሚ ኮሚቴው ማሳሰቡን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!