
ባሕር ዳር: ኅዳር 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በላሊበላ ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን እንዲጠበቁ እና በከተማዋ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳደሪ አራጌ ይመር የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች እናስመልሳለን በሚል አካሄድ ሌላ ችግር እንዲፈጠር እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች አሉት፤ ላለፉት ዓመታት ተበድሎ ቆይቷል፤ ነገር ግን ጥያቄዎችን በሕግና በሥርዓት ብቻ ነው ማስመለስ የሚቻለው ብለዋል። የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚመለሱት ከኢትዮጵያዊያን ጋር በጋራ በመኾን እንደኾነም ገልጸዋል።
የአማራን ሕዝብ ከሌሎች ነጥሎ ጥያቄን መመለስ እንደማይቻልም አመላክተዋል። ለኢትዮጵያ አንድነት እና ለሕዝብ እኩልነት በጋራ መሥራት ይገባልም ብለዋል። የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በተጀመሩበት የሰላም አማራጮች መመለስ አለባቸውም ብለዋል። ሰላማችን መልሰን አንድ መኾን ካልቻልን አንገታችንን እንደፋለን፣ ወደኋላ እንቀራለን ነው ያሉት። እርስ በእርሳችን በመገዳደል የምናስመልሰው የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የለም ብለዋል።
በአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ስም መነገድ እና የሕዝብን ሰላም መንሳት እንደማይገባም አመላክተዋል። የተፈናቀሉ ወገኖችን በሰላማዊ መንገድ ለመመለስ እየተሠራ መኾኑን የተናገሩት ዋና አሥተዳደሪው ሥራዎችን በሰላም ለመሥራት ሰላምን ማስቀደም ይገባል ነው ያሉት። የአባቶቻችን ጀግንነት እና የክብር ስም መጠበቅ፣ ባልተገባ መንገድ እንዳይውል ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
መንግሥት ማንንም ነጥሎ አልጠላም፤ ሊጠላም አይችልም፤ በነጻ አውጭ ስም የአማራን ሕዝብ ወደማያባራ ስቃይ እና እንግልት የሚከትቱትን ነው ያወገዝነው ብለዋል። የአባቶቻችንን ስም አናጉድፈው ነው ያልነው ብለዋል። ከሕመማችን እንድንድን እውነታውን ይዘን መታገል አለብን ነው ያሉት። በአንድነት ካልሠራን ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ካልተባበርን የከፋ ችግር ይገጥመናል ብለዋል። በተፈጠረው ችግር ሰዎች ሞተዋል፤ ንብረት ወድሟል፤ ከዚህ መውጣት አለብን ያሉት አሥተዳዳሪው ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ አለመኖሩንም ገልጸዋል።
ባልተገባ አካሄድ እና በሀሰተኛ መረጃ ከሚፈጠር ጥል እና ብጥብጥ መውጣት ይገባልም ብለዋል። የሀገር መከላከያ ሰራዊት የእኛ የኾነ፣ ለእኛ የሞተ፣ የተራበ አሁንም ለእኛ እየታገለ የሚገኝ የኢትዮጵያ ልጅ ነውም ብለዋል ዋና አሥተዳዳሪው። ተግባብቶ መሥራት እና በአንድነት መቆም እንደሚገባም ገልጸዋል።
ዋና አሥተዳዳሪው “ግጭት እና ጦርነት የአማራን ክብር ዝቅ ያደርጋል እንጂ ጥያቄዎቹን አያስመልስም” ነው ያሉት። የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን በጋራ መጠበቅ እንደሚገባም አሳስበዋል። እውነታውን በመረዳት ለእውነት መታገል እንደሚገባም አመላክተዋል። ችግሮቻችንን በምክክር እና በውይይት መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል። በመንግሥት በኩል ቅርሱ እንዲጠበቅ እንደሚሠራም አስታውቀዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!