
ባሕር ዳር: ኅዳር 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በላሊበላ ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የሰሜን ምሥራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ሻምበል ፈረደ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እየተዋጋ ያለው ከአማራ ሕዝብ ጋር ሳይኾን የአማራን ሕዝብ ሰላም ከሚነሱት ጋር ነው ብለዋል። ለሕዝብ የሚታገል እና ሕዝብ የሚያንገላታን አካል ጠንቅቆ መለየት እንደሚገባም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚዋጋ እንጂ የማንም ወገን አይደለም ብለዋል። ጀግና ያልኾነውን እንደጀግና ማንገሥ፣ ጀግና የኾነውን ማንኳሰስ ያልተገባ አካሄድ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአማራን ሕዝብ ስቃይ ማራዘም ትክክለኛ አካሄድ አይደለም ብለዋል። ለሕዝብ ክብር፣ ታሪክ፣ ሃይማኖት እና እሴት የማይመጥኑ አካሄዶችን መግራት እንደሚገባም አሳስበዋል። በሃይማኖት የጸኑ፣ ለሀገር ሰላም የሚቆሙ አባቶች እንዳሉ ሁሉ በሃይማኖት ስም የሚነግዱ አባቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል። የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት የመላው ዓለም ቅርስ መኾኑን የገለጹት ጄኔራሉ ቅርሱን በዓለም ፊት የምንኮራበት፣ የምንጠብቀው እና የምንቆረቆርለት ነውም ብለዋል።
“እኛ ሀገር፣ ሕዝብ እና ሃይማኖት እናከብራለን” ነው ያሉት። ቤተክርስቲያኗን ምሽግ ማድረግ እና በሃይማኖት ስም መነገድ እንዲቀርም አሳስበዋል። መከላከያ ሰራዊት ሃይማኖት እንደማያከብር፣ ቅዱስ ቦታ እንደሚያረክስ፣ የሕዝብ እሴት እንደሚጥስ ተደርጎ የሚወሰደው አሉባልታ መታረም እንደሚገባውም ተናግረዋል።
የአማራን ሕዝብ ጥያቄ በነፍጥ ማስመለስ እንደማይቻል ነው የተናገሩት። ለአማራ ሕዝብ እንታገላለን የሚሉት የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች ለማስመለስ አይደለም የሚታገሉት ያሉት ጄኔራሉ አካሄዱ ሕዝብ በእጁ የያዘውን ለማስጣል ነው ብለዋል። አማራ ዝቅ እንዲል፣ በሥነ ልቡና እንዲጎዳ እና በኢኮኖሚ እንዲወድቅ ማድረግ እንጂ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ እንዲመለስ ማድረግ አይችሉም፣ አይፈልጉምም ነው ያሉት።
የአማራ ሕዝብ አንድነት እንዲያጣ፣ ከሌሎችም ኢትዮጵያውያን እንዲነጠል ማድረግ እንደማይገባም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ወታደር በሕግና በሥርዓት የሚመራ መኾኑንም አስታውቀዋል።
የላሊበላን ቅርስ እንጠብቀዋለን፤ ላሊበላ የሀገር መኩሪያ እና መመኪያ ቅርስ ነውም ብለዋል። ለተቀደሰው ቦታ የተቀደሰ ተግባር እንደሚጠይቅም ገልጸዋል። ቅዱስ ሥፍራው እንኳን ሊተኮስበት ሊረግጡት የሚያሳሳ መኾኑንም ተናግረዋል። ብዝኀነትን እና አንድነትን ፀጋ አድርጎ መውሰድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የአማራን ሕዝብ ታላቅነት እና ሀገር ወዳድነት የሚመጥን ተግባር መከወን ይገባል ነው ያሉት። ሰላም የሚመጣው በአንድነት ስንቆም ነውም ብለዋል። በአንድ ወገን ብቻ የሚመጣ ሰላም አለመኖሩንም አመላክተዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት አንድ የኾነ፣ ለአንዲት ሀገር የቆመ፣ ለኢትዮጵያ የሚታገል መኾኑንም ገልጸዋል። የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ያልተገባ ስም መስጠት እና ማጠልሸት እንደማይገባም አመላክተዋል። የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሁሉም ለሁሉም መኾኑንም አንስተዋል። ቅርሱን እንጠብቀዋለን፣ እንቆረቆርለታለን፣ ነገር ግን በእኛ ስም ሊያሳብቡ የሚፈልጉትን በጋራ መታገል ይገባል ነው ያሉት።
ነገሮችን በብልሃት በመረዳት ብዙ ከመጥፋቱ በፊት ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም አመላክተዋል። የሃይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው ሁሉ በመምከር መመለስ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። “በእርግጠኝነት በእኛ ችግር አይፈጠርም፣ በእኛ ስም የሚነግዱትን ግን ታገሉ” ብለዋቸዋል። መከላከያ ሰራዊት ላይ ችግሮች ካሉ ፈጥነን እናርማለን፤ ተገቢውን ቅጣት እንቀጣለን፤ በእኛ ስም የሚነግዱትን፣ የእኛን ስም የሚያጠፉትን ግን ልትቆጣጠሯቸው ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!