
ባሕር ዳር: ኅዳር 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኪነ-ጥበብን ለሰላም ግንባታ እና የሕዝብን አብሮነት ለሚያጠናክሩ ጉዳዮች በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል አለብን ሲሉ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ ሰላም እና አንድነትን በማጠናከር ረገድ በሁለም የሥራ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች ኀላፊነት አለባቸው ብለዋል ባለሙያዎቹ፡፡
ኪነ-ጥበብ ሕዝብን ለሰላም እና ለአንድነት በጋራ ለማሰለፍ ትልቅ ሚና እንዳለውም የጥበብ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡ ተዋናይ ካሌብ ዋለልኝ ኪነ-ጥበብ እና ሰላም የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ሲል ተናግሯል፡፡ ከዚህ አኳያ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ሰላም፣ አንድነት እና ልማት እንዲመጣ ሕዝብን የማስተባበር ሚናችንን በአግባቡ መወጣት አለብን ነው ያለው፡፡
የዓድዋ ድልን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን በጋራ ያሳካናቸው ድሎች ሕዝብን ለማስተሳሰር ሚናቸው የጎላ ነው ብሏል። የጥበብ ባለሙያዎች እነዚህ አቅሞችን በመጠቀም ረገድ በርካታ ሥራዎች እንደሚጠበቅባቸውም ነው የተናገረው፡፡ ከዚህ አኳያ ለሰላም እና ለሕዝቦች አብሮነት መጠናከር ምን ያህል እየሠራን ነው ብለን መለስ ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ብሏል፡፡
ተዋናይ እና ገጣሚ ዋሲሁን በላይ ሀገር ለመገንባት ትውልዱ ላይ ጠንካራ የአገር ፍቅር ስሜት መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ተናግሯል። የበለጸጉ ሀገራት ትውልድን የቀረጹት በኪነ-ጥበብ መኾኑን ጠቅሶ፤ እኛም በዚህ ረገድ ብዙ መሥራት አለብን ነው ያለው፡፡ “በትብብር ሰላምን ማስፈን ፖለቲካ አይደለም” ያለው ተዋናይ ዋሲሁን፤ ከዚህ አኳያ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥቶ ተናግሯል፡፡
ሰላምና አንድነትን በማስፈን ረገድ የመገናኛ ብዙኀን እና የኪነ-ጥበብ ቤተሰቡ በቅንጅት መሥራት እንዳለበትም ጥሪ አቅርቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!