
አዲስ አበባ: ኅዳር 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)18ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የሚከበርባት የጅግጅጋ ከተማ በጋዜጠኞች እየተጎበኘች ነው፡፡
“ብዝኃነት እና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት በሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የሚከበረውን 18ኛው የብሔረሰቦች ቀን አሥመልክቶ የጋዜጠኞች ቡድን ወደ ክልሉ አቅንቷል።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት አሥተባባሪነት የተጓዘው ቡድኑ ዋና ዓላማው ለበዓሉ እየተደረገ ያለውን ዝግጅት እና የክልሉን የልማት እንቅስቃሴ መመልከት እና ለሕዝብ ማድረስ ነው ያሉት የክልሉ ኮሙኒኬሽን ምክትል ቢሮ ኀላፊ አቶ ፈርሃን ጅብሪል ናቸው።
ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የተውጣጣው የጋዜጠኞች ቡድን ከክልሉ ርዕሰ ከተማ ጅግጅጋ ወደ ጎዴ ከተማ ሲገባ የከተማው ከንቲባ አብዱላሂ ዓሊ ሐጂ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው ተቀብለዋል።
ከንቲባው ለጋዜጠኞች ባደረጉት ገለጻ በኢትዮጵያ ካሉ ትልልቅ ከተሞች የምትመደበዋ ጎዴ ከ250 ሺህ በላይ ሕዝብ የሚኖርባት ከተማ ናት ብለዋል።
በከተማዋ በርካታ የልማት ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት ከንቲባው ጥቂቶቹን ተዘዋውረው አሥጎብኝተዋል። ከተጎበኙት ውስጥ 475 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የጎዴ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ይገኝበታል።
የሸበሌ ወንዝ ላይ የተሠራው ፕሮጀክቱ ከ6 ሺህ በላይ ሕዝብ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
የአረንጓዴ ልማት፣ የሆስፒታል ግንባታ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ እንዲኹም የመንገድ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው። በመንገድ በኩል 2 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር መንገድ መገንባት መቻሉን የኮሙዩኒኬሽን ኀላፊው ተናግረዋል፡፡ ይህም ካለፉት 50 ዓመታት በተሻለ መንገድ ባለፉት 5 ዓመታት በብዛት መገንባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!