ሌላ ጫና አንችልም፤ ሰላም ነው የምንፈልገው” የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች

28

ወልድያ: ኅዳር 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ ነው።

በውይይቱ የሰሜን ወሎ ሀገረ ሥብከት ሊቀ ጳጳስ እና የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፣ የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው(ዶ.ር)፣ የሰሜን ምሥራቅ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ሻምበል ፈረደ፣ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳደሪ አራጌ ይመርን ጨምሮ የዞን እና የወረዳ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች በውይይታቸው ዘላቂ ሰላም እንደሚሹ እና ከግጭት እንዲወጡ እንዲሠራ ጠይቀዋል። በላሊበላ ከተማ በተፈጠረ ግጭት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል።

የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትም እንዳይጎዱ ሥጋት እንዳለም ሲነገር ቆይቷል። ነዋሪዎቹ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር እና የተቀደሰው ቅርስ እንዲጠበቅ ዘላቂ እና አሥተማማኝ ሰላም እንዲኖር ጠይቀዋል።

እርስ በእርሳችን እየተባላለን ለጠላት ምቹ እየኾንን ነው ብለዋል። ችግር ከመፈጠሩ፣ ሰው ከመሞቱ እና ንብረት ከመውደሙ አስቀድሞ ለሰላም መሥራት እንደሚያሥፈልግም ገልጸዋል። በተቀደሰች ሀገር፤ በተቀደሰ ቦታ እየኖርን የተጠላ እና ሰውን የሚያጠፋ ሥራ መሥራት እንደማይገባም ተናግረዋል።

“ችግሩን በሰላም ፍቱልን፣ ድኅነቱ ይበቃናል፣ ሰላም ነው የምንፈልገው፣ ልጆቻችን እናስተምር” ነው ያሉት ነዋሪዎቹ። አሁን ያለው ጦርነት እየገባን አይደለም፣ ወንድም ከወንድሙ ጋር መዋጋት እና ለግድያ መፈላለግ አይገባውም ብለዋል።
ወንድም ወንድሙን መግደል አንገት እንደሚያሥደፋም ተናግረዋል። መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ ሠጥቶ እንዲሠራም ጠይቀዋል።

ስለ ሰላም አርፍደናል፣ ነገር ግን ከመቅረት ይሻላል፣ በተደጋጋሚ መሞት አንፈልግም በውይይት ይፈታ ነው ያሉት ተወያዮቹ። ከድኅነት በላይ ሌላ ጫና መሸከም አንችልም ነው ያሉት። እንኳን ጦርነት ተጨምሮበት ድኅነቱ እና የኑሮ ጫናውን አልቻልነውም ይበቃናልም ብለዋል።

በዓለም ላይ የሌለ ቅርስ እና ቅዱስ ቦታ ይዘን ደም መፋሰስ እንዲኖር መፈቅድ አይገባም ነው ያሉት። በከተማዋ እና በአካባቢው ያልተገቡ አሉባልታዎች ለግጭት እያደረጉ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ ለሰላም የሚሠሩ አባቶች እየተከበሩ አለመኾናቸውንም ገልጸዋል። ለታሪክ የማይመጥን ለቅዱስ ቦታ የማይገባ ተግባር እንዳይፈጸም መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት የቱሪዝም ሃብት ናቸው። በእርሱ በረከት መኖር ይገባናል እንጂ ትክ የለሹን ቅርስ አደጋ ውስጥ ማስገባት ተገቢ አይደለም ነው ያሉት።

ለቅርሱ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግም ጠይቀዋል። የፖለቲካ መሪዎችም ሰላምን መስበክ እና ሰላምን ማስፈን እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። በከተማዋ ያለው ሕገ ወጥ አካሄድ እና ዝርፊያ እንዲቆምም ጠይቀዋል።

ሳይሰለቹ መወያየት፣ መግባባት እና ችግሮችን በአንድነት መፍታት ይገባል ነው ያሉት። ቅርሱን ለመጠበቅ፣ የሰው ሕይወትን ለመታደግ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መወያየት እና መመካከር ይገባል ነው ያሉት።

ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ካልተቻለ የሚመጣ ሰላም እንደሌለም ተናግረዋል። መንግሥት ሕዝብ የሚያነሳቸውን የመፍትሔ ሀሳቦች በመውሰድ መተግባር እንደሚገባም ገልጸዋል። ለግጭት መነሻ የኾኑ ችግሮችን ማድረቅ እና ጥያቄዎችን መመለስ እንደሚገባው አመላክተዋል።

በከተማዋ የቱሪዝም እንቅስቃሴ በመቆሙ ነዋሪዎች ችግር ላይ መውደቃቸውን ተናግረዋል። አካባቢው በጦርነት የተጎዳ እንደመኾኑ መጠን በዘላቂነት ከጦርነት የሚያወጣ መፍትሔ እንሻለን ብለዋል።

ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ አለመኖሩን ሁሉም ሊረዳው እንደሚገባም ገልጸዋል። የጋራ ችግሮች እንዳሉ ሁሉ የጋራ መፍትሔ ማምጣት እንደሚገባም አመላክተዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮ-ቴሌኮም ቀላል እና ምቹ የትራንስፖርት እና ነዳጅ አቅርቦትን የሚያዘምን ሶሊሽን ይዞ መምጣቱን አስታውቋል።
Next articleየሸበሌ ወንዝ ላይ የተሠራው ፕሮጀክቱ ከ6 ሺህ በላይ ሕዝብ ተጠቃሚ ያደርጋል ተባለ።