
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ገለጸ።
አዲስ አበባ: ኅዳር 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአገልሎት ተደራሽነትን ለማዘመን ዘርፉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ገልጿል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ከፓስፖርት አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ስላሉ አፈጻጸሞች፣ እየተወሰዱ ስላሉ እርምጃዎች እና ችግሮችን ለመቅረፍ እየተተገበሩ የሚገኙ አሠራሮችን በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል።
ዳይሬክተሯ በመግለጫቸው ተቋሙ ከ100 ቀን እቅዶቹ ውስጥ በሦስት ወራት የተከናወኑ ተግባራትን አንስተዋል።
በሦስት ወራት ውስጥ ከ290 ሺህ በላይ የፓስፖርት ቡክሌቶች ታትመው ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል። ስድስት ወር የቆዩ ፓስፖርቶችን ቅድሚያ በመስጠት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል።
ፓስፖርት ለደረሰላቸው ዜጎች ጥሪ በማድረግ እንዲወስዱ አድርገናልም ብለዋል። ጥሪ ከተደረገላቸው ውስጥ 30 በመቶ የሚኾኑት በወቅቱ ተገኝተው መውሰድ አልቻሉም ነው ያሉት።
አስቸኳይ ፓስፖርት ለሚፈልጉ ዜጎች ቅድሚያ በመስጠት በሀገር ውስጥ ታትሞ መሰራጨቱንም በመግለጫቸው ጠቁመዋል። ከ40 ሺህ በላይ የሚኾኑ በውጪ ሀገር የሚኖሩ ዜጎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ስለመቻሉም ተናግረዋል።
ዳይሬክተሯ በተቋሙ ውስጥ በሌብነት እና ብልሹ አሠራሮች የተጠረጠሩ ግለሰቦች በክትትል ተለይተው ጉዳዩ እየተጣራ ነው ብለዋል። በዚህ ጉዳይ 52 ሰዎች ተይዘው ጉዳያቸው በሕግ እየታየ መኾናቸውን ነው ወይዘሮ ሰላማዊት የጠቀሱት።
180 የሚኾኑ የውጪ ሀገር ዜጎች ሕገ ወጥ ሰነዶችን በመያዝ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተው በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- አየለ መሥፍን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!