ትምህርት ቤቶችን እና ተማሪዎችን ሁሉም አካል ይደግፍ” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ

41

ባሕር ዳር: ኅዳር 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

ከ256 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች ማሰራጨቱን ቢሮው አስታውቋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለማሻሻል እና የትምህርት ግብዓት ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች የጽሕፈት መሳሪያ ለማሟላት ዘመቻ አካሂዷል። ሐምሌ /2015 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ “ትምህርት ለትውልድ” በሚል መሪ መልዕክት ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት የንቅናቄ መርሐ ግብር ማካሄዱ ይታወሳል።

ባለፉት አራት ወራት ትምህርት ቢሮን ጨምሮ ከማኅበረሰቡ፣ ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ተቋማት 256 ሚሊዮን በላይ ብር ድጋፍ መገኘቱ ተገልጿል።

የተገኘውን ቁሳቁስ ለተቸገሩ ተማሪዎች ማሰራጨቱን በቢሮው የትምህርት ቤት ማሻሻል ዳይሬክተር ሕብስቴ ካሴ ገልጸውልናል።

ደብተር፣ እስክብሪቶ፣ እርሳስ፣ ቦርሳ እና ዩኒፎርም ለ278 ሺህ 806 ተማሪዎች ተዳርሷል ብለዋል።

ከተሰራጨው የጽሕፈት መሳሪያ ውስጥ ደግሞ 61 በመቶው ደብተር እንደኾነ ገልጸዋል።

ዳይሬክተሯ እንዳሉት በትምህርት ቢሮ በተመደበ 174 ሚሊዮን ብር 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ደብተር በግዥ ሂደት ላይ ይገኛል፤ ለ300 ሺህ ተማሪዎችም ተደራሽ ይኾናል።

በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በታሰበው ልክ እንዳይሠራ ማድረጉም ተነስቷል። በቀጣይ ሰላሙ ሙሉ በሙሉ ሲመለስ ተግባሩ በተጠናከረ መንገድ ይቀጥላል ተብሏል።

በሥነ-ምግባሩ የታንጸ እና ውጤታማ ትውልድ ለማፍራት ማኅበረሰቡ፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ትምህርት ቤቶችን እና የተቸገሩ ተማሪዎችን እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል ዳይሬክተሯ።

ወላጆች እና ማኅበረሰቡ የመማር ማስተማር ሂደቱን እንዲከታተሉም አሳስበዋል ።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአኩሪ አተርን ምርት እና ጥራት በማሻሻል ተገቢውን የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሚገባ ተገለጸ።
Next articleየአገልሎት ተደራሽነትን ለማዘመን እየሠራ መኾኑን