የአኩሪ አተርን ምርት እና ጥራት በማሻሻል ተገቢውን የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሚገባ ተገለጸ።

58

አዲስ አበባ: ኅዳር 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እና ለውጭ ሀገር ገበያ ቀርቦ ለውጥ ማምጣት የሚችለውን የአኩሪ አተርን ሰብል ምርት እና ጥራት በማሻሻል ተገቢውን የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሚገባ ተገልጿል።

የአኩሪ አተርን ምርት እና ጥራት በማሳደግ የገበያ ትስስርም መፍጠር የሚያስችል የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ ተካሄዷል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን በ2015/2016 የምርት ዘመን 340 ሺህ ሄክታር ማሳ 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል የአኩሪ አተር ምርት ተገኝቷል ብለዋል። ከዚህ ውስጥም 240 ሺ ሄክታሩ በአማራ ክልል የተሸፈነ ነው ብለዋል።

በዘንድሮው ዓመትም 400 ሺህ ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር ምርት መሸፈኑን እና ከዚህም 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ በልሁ ተሻገር የአኩሪ አተር ምርትን ለማሻሻል አርሶ አደሩን በቅርበት ኾኖ በግብዓት እና በሙያ ማገዝ እና ተባብሮ መሥራት ይገባል ብለዋል። የቅባታማ እህሎች ላይ በትኩረት መሠራቱ የሀገር ውስጥ ፍጆታን ለመተካት እና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እንደሚያስችልም ጠቅሰዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው ሐሰን መሐመድ ዘርፉ ለወጣቶች እና ለሴቶች ከፍተኛ የሥራ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

በምክክሩ ላይ በአኩሪ አተር ምርት ዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ተነስተው በመፍትሔ ሀሳቦች ላይም ውይይት ተደርጓል።

በምክክር መድረኩ የኢንደስትሪ ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እንዲሁም የቅባት አህል አምራች ማኅበራት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ:- ቤቴል መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፖለቲካ ወንጀሎች የሀገር ስጋት እየሆኑ መምጣታቸው ተገለጸ።
Next articleትምህርት ቤቶችን እና ተማሪዎችን ሁሉም አካል ይደግፍ” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ