
አዲስ አበባ፡ ኅዳር 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ማስተግበሪያ ሰነድ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ወይይት እያደረጉ ነው።
በውይቱ ላይ የተገኙት የፍትሕ ሚኒስትር፣ የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደው፤ ወንጀልን በየትኛውም ዓለም ማጥፋት ባይቻልም አስቀድሞ በመከላከል መቀነስ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ይህንን ለመከላከል ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ከነደፈች በኃላ የማስፈፀሚያ ሰነድ ተዘጋጅቷል። ይህንን የሚከታተል በኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር እና በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። ዛሬም በዚህ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ ግብዓት እንወስዳለን ብለዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ፤ ወንጀል የሰውን ልጅ ማኅበራዊ ኑሮ የሚፈትን ተለዋዋጭ የኑሮ ተግዳሮት ነው።
አሁን ላይ ደግሞ ከማኅበራዊ ወንጀሎች በላይ የፖለቲካ ወንጀሎች ተበራክተው ይስተዋላሉ ብለዋል።
እነዚህ የፖለቲካ ወንጀሎችን በጊዜ እና በአግባቡ መቆጣጠር ካልተቻለ ደግሞ ሀገርን የማፍረስ እድል አንዳላቸው የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎች ያሳያሉ።
ይህን ለመከላከል በ2012 ዓ.ም የወጣውን ስትራቴጂ መሰረት አድርጎ ዛሬ በማስፈፀሚያ ሰነድ ስልት ላይ እንደሚመከርም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!