
ወልድያ፡ ኅዳር 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በላሊበላ ከተማ አሥተዳደር የሰላም ውይይት እየተካሄደ ነው። ውይይቱ በከተማዋ ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት በመፍታት ሰላም ለማስፈን ያለመ ነው። በውይይቱ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፣ የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)፣ የሰሜን ምሥራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ሻምበል ፈረደ፣ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳደሪ አራጌ ይመርን ጨምሮ የዞን እና የወረዳ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ወንድምነው ወዳጅ በዚህ በመከራ ጊዜ ልናስተባብር የመጣን እንጂ ተመችቶን ልንኖር የምንሻ አይደለንም፣ በፈተና ወቅት ከሕዝብ ጎን በመኾን በሕዝብ ላይ የገጠመውን ችግር ለመፍታትም እየጣርን ነው ብለዋል። ሕዝቡም ከጎናችን በመኾን አጥፊዎችን ለይቶ መታገል ይገባዋል ነው ያሉት።
ሰላም የሚመጣው በራሱ በሰላም ብቻ መኾኑም ተናግረዋል። ደም መፋሰስን የሚያቆሙ አባቶች እንዳይኖሩ የማድረግ ስብከት መቆም እንደሚገባውም አመላክተዋል። መሪ እንዳይኖር የሚደረጉ ሥራዎችም መታረም አለባቸው ብለዋል። በአንድነት መቆምና መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ከእውነት ይልቅ ውሸት እና አሉባልታ የሚያናፍስን አካል ማውገዝ እንደሚገባም ገልጸዋል። ብዙዎች መጥተው የሚማፀኑባት ከተማ የደም መፋሰሻ እንዳትኾን መሥራት ይገባል ነው ያሉት። አካባቢውን፣ ታሪኩን እና እሴቱን የሚመጥን ሆነን መገኘት አለብንም ብለዋል።
ሰላምን በመስበክ ሀገራዊ አጀንዳ ላይ መወያየት እንደሚገባም ተናግረዋል። ሀገረዊ ጉዳይን እንደቀላል ማየት ለውድቀት እንደሚዳርግም ገልጸዋል። ከተማዋ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነበት፣ አሉባልታ የሚርቅባት፣ አስጸያፊ የሆነ ነገር ሁሉ የሚወገድባት እንድትኾን እንፈልጋለን፤ ትክክለኛ የቅዱሳን ቦታ መኾኑን የምናስመሰክር ለቦታውም የምንመጥን ሆነን መገኘት አለብንም ብለዋል።
ለመፍትሔው ራስን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል። ከተማዋ ሰላም እንዳታጣ ማድረግና በገራ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል። “ብዙዎች የሚናፍቁትን ቅዱስ ቦታ የደም መፋሰሻ እንዳይኾን መሥራት ይገባል” ሲሉም ከንቲባው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!