
ደሴ: ኅዳር 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወቅታዊ ኹኔታ እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር የውይይት መድረክ በደሴ ከተማ ተጀምሯል። በውይይቱ ላይ የሚሳተፉት ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች እንዲሁም የደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎና ዋግኽምራ ዞኖች አጠቃላይ መሪዎች ናቸው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ሰላም የሚሰፍነው በሁሉም ተሳትፎና ጥረት ነው ሲሉ አስገንዝበዋል። ይህንን በመገንዘብም አመራሩና መላው ሕዝብ ለክልሉ ሰላም በቁርጠኝነት መሥራት አለበት ብለዋል።
በውይይት መድረኩ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርጉ አሥፈላጊ ነገሮች ተነስተው ቀጣይ መደረግ ስለሚገባው ጉዳይም ምክክር እንደሚደረግ ተገልጿል።
ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ “ለሰላም ለመሥራት ሀቀኝነትን እንጂ አስመሳይነትን አይፈልግም” ሲሉም ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ እንደከተማ አሥተዳደር አመራሩ ሕዝቡን ቀርቦ በማወያየት የሰላም ባለቤትና ጠባቂ እንዲኾን እየተደረገ ነው ብለዋል። በክልሉ ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ ሕዝቡም በሙሉ አቅሙ ወደ ልማት መግባት እንዲችል የሚጠበቅባቸውን የአመራርነት ሚና ለመወጣት ዝግጁ ስለመኾናቸውም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ:- ከድር አሊ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!