
ባሕር ዳር: ኅዳር 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጀርመኑ ዩኒየን በርሊን ክለብ በሀገሪቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ምክትል አሠልጣኝ መሾሙን አስታውቋል።
በጀርመን ቡንደስሊጋ እየተሳተፈ የሚገኘው የዩኒየን በርሊን አሠልጣኝ ኡርስ ፊሸርን ከአምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ አሰናብቷል፡፡
ለአሠልጣኙ መነሳት ምክንያቱ ደግሞ ክለቡ በዚህ የውድድር ዘመን እስካሁን አስራ አንድ ጨዋታዎችን አድርጎ በዘጠኙ መሸነፉ ነው ተብሏል፡፡
ከተመሰረተ 117 ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ አንጋፋ ክለብ ታዲያ በጀርመን ቡንደስሊጋ ሴት አሠልጣኝ በመሾም ታሪክ መሥራቱን ዘ- ሰን ዘግቧል።
ሜሪ-ሉዊዝ ኢታ ትባላለች አሠልጣኟ፤ በተጫዋችነት ሕይዎቷ በክለብ ደረጃ ለአራት ቡድኖች ተጫውታለች። በ177 ጨዋታዎች ተሰልፋ በመጫወት ሰላሳ ግብ ማስቆጠር የቻለች ናት፡፡
ለሀገሯ ጀርመን ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ሃምሳ ጨዋታዎችን አድርጋ ዋንጫ አንስታለች፡፡
የ32 ዓመቷ ኢታ በቡንደስሊጋው ታሪክ ጨዋታዎችን በመምራት የመጀመሪያዋ ሴት አሠልጣኝ ትኾናለችም ነው የተባለው፡፡
ሜሪ-ሉዊዝ ኢታ ከዚህ ቀደም በጀርመን ከ15 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ረዳት አሠልጣኝ ኾና መሥራቷንም ሮይተርስ አስታውሷል፡፡
አሁን ደግሞ በዩኔን በርሊን የአሠልጣኝ ብረንደን አሮንሰን ምክትል ኾና በመሾም በጀርመን እግር ኳስ ታሪክ ቀዳሚ ኾናለች።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!