
ባሕር ዳር: ኅዳር 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በቀጣይ ዓመት ከ200 በላይ የመሥኖ ፕሮጀክቶችን ለማልማት መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ከ110 በላይ የመሥኖ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውን የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ አሥታውቋል፡፡
አርሶ አደር ዓለሙ ወሌ በዳንግላ ወረዳ ውንብሪት ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር ዓለሙ በመስኖ የሚያለሙት ከሁለት ሔክታር በላይ መሬት አላቸው፡፡
ባላቸው መሬት ላይ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ጥቅል ጎመን፣ ሸንኮራ አገዳ፣ ገብስ እና በቆሎ ያመርታሉ፡፡ በቅርቡ የተጠናቀቀው “ውንብሪት የመሥኖ ፕሮጀክት” ከግማሽ ሔክታር በላይ መሬታቸውን ተደራሽ እንደሚያደርግላቸው ገልጸዋል፡፡ ቀሪውን በመሬታቸው አካባቢ በምትገኝ ምንጭ በጀኔሬተር በመሳብ እንደሚያለሙ ተናግረዋል፡፡
የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ለአካባቢው ማኅበረሰብ አዲስ ብስራትን ይዞ እንደመጣም ገልጸዋል፡፡ ተደራሽ የኾኑ አርሶ አደሮች ማሳቸውን እያለሰለሱ ነው፡፡ ግብዓት ሲመጣ ወደ ዘር እንገባለን ብለዋል፡፡
ቄስ መኳንንት አላምረው በዳንግላ ወረዳ ውንብሪት ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ቄስ መኳንንት በመስኖ የሚያለሙት ሦስት ገመድ መሬት አላቸው፡፡ ጄኔሬተር በመጠቀም ሥንዴ እና በቆሎ ሲያመርቱ ቆይተዋል፡፡
በ2015 ዓ.ም የተጠናቀቀው የውንብሪት የመስኖ ፕሮጀክት ችግራቸውን ቀርፎላቸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ካመረቱን ሰባት ኩንታል ስንዴ እና አራት ኩንታል በቆሎ የተሻለ ለማምረት ማሳቸውን አለስልሰው የግብዓት መምጣትን እየተጠባበቁ መኾኑን ነግረውናል፡፡ በዚህ ዓመት በርካታ አርሶ አደሮች ወደ መስኖ እንደሚገቡም አንስተዋል፡፡
የዳንግላ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አያና አቤ በወረዳው የተገነባው “ውንብሪት የመስኖ ፕሮጀክት” ከስምንት መቶ ሔክታር በላይ መሬት ሊያለማ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የተጠናቀቀው የመስኖ ፕሮጀክት የወረዳውን በመስኖ የመልማት አቅም ወደ 3 ሺህ 580 ሔክታር ከፍ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የዳንግላ ወረዳን እና የደቡብ ሜጫ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል ያሉት ኀላፊው ከ1 ሺህ 500 በላይ አርሶ አደሮችን በአዲስ ተጠቃሚ እንደሚያደግም ገልጸዋል፡፡
አቶ አያና ቀሪዎቹ አርሶ አደሮች ትልልቅ የውኃ መሳቢያ ጀኔሬተሮችን ተጠቅመው እያለሙ መኾኑን አንስተዋል፡፡ እነዚህን አርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ የተያዙ ሌሎች ፕሮጀክቶች ቢኖሩም በመጓተታቸው አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ አለማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡
በአማራ ክልል የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ መስኖ እና ድሬንኤጅ ግንባታ ክትትል ዳይሬክተር ጌትነት አያሌው በ2015 ዓ.ም 117 የመሥኖ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከተጠናቀቁት ውስጥ ሰባቱ ጥገና እና 110 የመስኖ ፕሮጀክቶች ደግሞ በአዲስ የተገነቡ ናቸው፡፡ የተጠናቀቁት የመስኖ ፕሮጀክቶች ከ7 ሺህ 600 ሔክታር በላይ መሬት ያለማሉ ተብሎ በእቅድ መያዙን ገለጸዋል፡፡
ፕሮጀክቶችን ሠርቶ ለማጠናቀቅ 786 ሚሊዮን ብር ወጭ እንደተደረገባቸው አቶ ጌትነት ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ አነስተኛ እና መካከለኛ የሚባሉ ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ በአግባቡ ከተያዙ እና ተገቢው እንክብካቤ ከተደረገላቸው ከ10 እስከ 25 ዓመታት ሊያገለግሉ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች ከወንዝ የተጠለፉ መኾናቸውንም አቶ ጌትነት ገልጸዋል፡፡ ሥርጭታቸውም ፍትሐዊነትን ያማከለ እንደኾነ ጠቅሰዋል፡፡
የፕሮጀክቶቹ የበጀት ምንጭ የፌዴራል መንግሥት፣ መደበኛ የክልሉ መንግሥት በጀት፣ ረጅ ድርጅቶች እንዲኹም የማኅበረሰቡ ተዋጽኦን ያማከለ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይ ዓመት ከ200 በላይ የመሥኖ ፕሮጀክቶችን ለማልማት መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!