“ከታተሙ መጻሕፍት ውስጥ 56 በመቶ ትምህርት ቤቶች ላይ ደርሰዋል” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ

32

ባሕር ዳር: ኅዳር 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል 7 ሚሊዮን 462 ሺህ በላይ መጻሕፍት ታትመዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 56 በመቶ የሚኾነው ትምህርት ቤቶች ላይ መድረሱን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡

7 ሚሊዮን 462 ሺህ 667 የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የአንደኛ ደረጃ መጻሕፍት እስከ ሐምሌ/2015 ዓ.ም መጨረሻ በደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ጎንደር፣ ደብረ ማርቆስ እና ወልድያ የክዘና ማዕከላት መግባቱን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ ዳይሬክተር ካሴ አባተ ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ ታትሞ ወደ ክልሉ ከገባው መጻሕፍት ውስጥ እስከ ሕዳር 4/2016 ዓ.ም ድረስ 56 በመቶ የሚኾነው ወደ ትምህርት ቤቶች ተሰራጭቷል።

ከአምስቱ የክዘና ማዕከላት ውስጥ በደሴ ማዕከል 91 በመቶ፣ በወልድያ ማዕከል 73 በመቶ፣ በጎንደር ማዕከል 81 በመቶ፣ በደብረ ብርሃን ማዕከል ደግሞ 64 በመቶ የሚኾነው መጻሕፍት ተሰራጭቷል።

በደብረ ማርቆስ ክዘና ማዕከል ከሚገኘው 2 ሚሊዮን 274 ሺህ 565 መጻሕፍት ውስጥ 35 ሺህ መጻሕፍት ብቻ ነው በደብረ ማርቆስ በከተማ አሥተዳደር ማሰራጨት የተቻለው።

በዚህ ዓመትም ከዚህ በፊት ያልታተሙ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ የመማሪያ እና የማስተማሪያ መጻሕፍት በሀገር ውስጥ በመታተም ላይ እንደሚገኙ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። የታተሙት መጻሕፍት 1 ለ 2 እና 1 ለ 3 ተደራሽ እንደሚኾኑ ገልጸዋል።

የ2ኛ ደረጃ መማሪያ መጻሕፍት ደግሞ በፌዴራል ደረጃ መታተሙን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። እስከ ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም ለማቅረብ ቢታሰብም እስካሁን በጎንደር የክዘና ማዕከል መግባት የቻለው 375 ሺህ 348 የ9ኛ ክፍል 5 የትምህርት ዓይነቶች መጻሕፍት ብቻ ናቸው። ይህም አጠቃላይ ወደ ክልሉ መድረስ ከነበረበት 19 በመቶ ገደማ ብቻ መኾኑ ተገልጿል። ትምህርት ቢሮም ድልድል መሥራቱን ነው ያነሱት።

የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ ከሚያሥፈልጉ መሥፈርቶች የመጻሕፍት አቅርቦት ቀዳሚውን ደረጃ እንደሚይዝ ያነሱት ዳይሬክተሩ የመማሪያ መጻሕፍት በወቅቱ ባለመቅረቡ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል።

የትምህርት ሥርዓቱ አዲስ እንደመኾኑ ይዘቱን ጠብቆ የተዘጋጀ የማጣቀሻ መጽሕፍት አለመኖር በተለይም ደግሞ በገጠራማው የክልሉ አካባቢ በመማር ማስተማር ሥራው ላይ ትልቅ እንቅፉት እንደፈጠረ አንስተዋል፡፡

ተማሪዎች ከድሮው የትምህርት ሥርዓት ጋር የሚመሳሰሉ ይዘቶችን እንዲያነቡ እና የተለያዩ አማራጮችን እንዲጠቀሙ መምህራን እንዲያግዙ ጠይቀዋል።

መንግሥትም መጻሕፍትን በአጭር ጊዜ ወደ ክዘና ማዕከላት እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ደረጃቸውን የጠበቁ የትምሕርት ተቋማትን መገንባት ብቁ የኾነ የሰው ኃይልን ለማፍራት የላቀ አስተዋጽኦ አለው” ምክትል ርእሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን
Next articleየኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቅሬታውን ለፊፋ አቀረበ።