“ደረጃቸውን የጠበቁ የትምሕርት ተቋማትን መገንባት ብቁ የኾነ የሰው ኃይልን ለማፍራት የላቀ አስተዋጽኦ አለው” ምክትል ርእሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን

43

ጀሴ፡ ኅዳር 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን 116 ሚሊየን ብር ወጭ ተደርጎ በሰዎች ለሰዎች ድርጅት የተገነባው የጃማ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

ሰዎች ለሰዎች ድርጅት በጀርመን መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የጃማ ነው ቴክኒክና ሙያ ኮሌጁን ገንብቶ ያጠናቀቀው። 116 ሚሊየን ብር ወጭ የተደረገው ለግንባታ እና የውስጥ ቁሳቁሱን ለማሟላት ነው ተብሏል።

የተገነባው ኮሌጅ በዞኑ ያሉት የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆችን ቁጥር አስራ አምስት አድርሷል። በጀርመን የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ሰባስቲያን ብራንዲስ (ዶ/ር) ድርጅቱ ተደራሽነቱ እና የመፈጸም አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው ብለዋል። ድርጅቱ በኢትዮጵያ የትምህርት መሰረተ-ልማት ግንባታዎች ላይ የጎላ ድርሻ እንዳለውም አንስተዋል። እስካሁን ድረስ በሀገሪቱ በአጠቃላይ 466 ትምሕርት ቤቶችን ከነመማሪያ ቁሳቁሶቻቸው መገንባቱንም አንስተዋል። ሰባት የቴክኒክ ሙያ ትምህርት ማሰልጠኛዎችንም ከነመማሪያ ማሽኖች አስገንብቶ ለሕዝብ እና መንግሥት ማስተላልፉን አስረድተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ አቶ ደምስ እንድሪስ ሰዎች ለሰዎች ድርጅት ጥራቱን የጠበቀ ኮሌጅ ገንብቶ ማስረከቡ በዞኑ ያለውን የኮሌጅ እጥረት ይቀርፈዋል ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ድርጅቱ ለኮሌጁ መምህራን ሥልጠና እየሰጣቸው እንደኾነ አንስተዋል።

የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ/ር) ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ብቁ ባለሙያ ማፍራት እደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ደረጃቸውን የጠበቁ ግንባታዎች እና ዘመናዊ ማሽነሪዎች ሊሟሉ ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ተወዳዳሪ ኮሌጅን ከነሙሉ ማሽነሪው ገንብቶ እና አደራጅቶ በማስረከቡ ሊመሰገን ይገባዋል ብለዋል ቢሮ ኀላፊው፡፡

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን “ደረጃቸውን የጠበቁ የትምሕርት ተቋማትን መገንባት ብቁ የኾነ የሰው ኃይልን ለማፍራት የላቀ አስተዋጽኦ አለው” ብለዋል፡፡ ሰዎች ለሰዎች ድርጅት ላደረገው እገዛ አመስግነው ይህን መሰል በጎ ተግባር በሌሎች አካባቢዎችም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ሲል የደቡብ ወሎ መንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በውይይትና በመግባባት እንጂ በአፈሙዝ የሚፈታ የሕዝብ ጥያቄ የለም” የደሴ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ አባላት
Next article“ከታተሙ መጻሕፍት ውስጥ 56 በመቶ ትምህርት ቤቶች ላይ ደርሰዋል” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ