
ባሕር ዳር: ኅዳር 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በተዋበች ሀገር ምንትዋብ ነገሡባት፤ በተዋበው ዙፋን ምንተዋብ ተቀመጡበት፤ የተዋበውን ዘውድ ምንትዋብ ደፉት፣ የተዋበውን በትረ መንግሥት ምንተዋብ ጨበጡት፤ የተቀደሰውን ቅበዓ ቅዱስ ምንትዋብ ተቀቡት፤ በተዋበው ቤተ መንግሥት በአስፈሪ ግርማ ምንትዋብ ኖሩበት፤ የተዋበውንም ቤተ መንግሥት ምን ትዋብ አሠሩት፤ የተቀደሰችውን ሀገር ምንትዋብ አሥተዳደሯት፤ በቃል ኪዳን ተቀብለው በቃል ኪዳን ጠበቋት፤ በቃል ኪዳንም ለልጅ ልጆቻቸው አስተላለፏት፡፡
ስምን መላዕክ ያወጠዋል ይሉት ግብር ተገለጠባቸው፤ ከዘመን ዘመን የማይደበዘዝ ግርማ ተሰጣቸው፤ ዘመናት ሲያልፉ የማይኮሰምን የሰው ፍቅር ተቸራቸው፡፡ ተውበው ተወልደው፣ ተውበው ኖረዋልና ሁሉም ምንትዋብ ይላቸዋል፡፡
ገና በማለዳው በስም ያማሩ፣ በምግባር የከበሩ፣ በግርማ የኖሩ፣ አያሌ ታሪኮችን የሠሩ እመቤት ናቸው፡፡ በአማረው ዙፋን ላይ ተቀምጠው፣ በአልማዝ ባጌጠው ካባ ተንቆጥቁጠው፣ እጹብ የሚያሰኘውን በትረ መንግሥት ጨብጠው፣ መኳንንቱ እና መሣፍንቱ ከበዋቸው፣ እልፍ በቀኝ፣ እልፍ በግራ፣ እልፍ በኋላ፣ እልፍ በፊት እጅ እየነሳላቸው፤ ካማረው ቤተ መንግሥት በወጡ ጊዜ ለእግራቸው መረጋጋጫ የወርቅ ምንጣፍ እየተዘረጋላቸው፣ ለክብራቸው እልል እየተባለላቸው፣ በእንቁ ያጌጠ ሰረገላ እተየዘጋጀላቸው በከፍታ ኖረዋል እቴጌ ምንትዋብ፡፡
እቴጌዋ በአልማዝ ማጌጡ፣ በእንቁ መንቆጥቆጡ፣ በአስፈሪ ዙፋን መቀመጡ፣ እጹብ የሚያሰኝ በትረ መንግሥት መጨበጡ አኩርቷቸው፣ አስመክቷቸው፣ ዘመናቸውን በደስታና በፌሽታ ብቻ አላሳለፉም፡፡ ይልቅስ ስማቸው የሚታወስበትን፣ ክብራቸው የሚነግረበትን፣ ዘመናቸው የሚዘከርበትን ታላቅ ታሪክ ሠሩ፤ ሀገራቸውን ዘለግ ላሉ ዓመታት በብልሃት፣ በታማኝነት፣ በጀግንነት አሥተዳደሩ እንጂ፡፡
ምንትዋብ ስማቸው ብቻ አይደለም፤ ግብራቸው፣ ታሪካቸው እና አሻራቸው ሁሉ የተዋበ ነው እንጂ፡፡ በሴት ስም በምትጠራው ጥንታዊት ሀገር ኢትዮጵያ ትናንት ላይ ቆመው ዛሬ እና ነገን የሚተነብዩ ትንቢተኛ፣ የማይቻል የሚስለውን የሚችሉ ጥበበኛ፣ የሴት ነገሥታት ስም በተጠቀሰ ቁጥር የእርሳቸው ስምም ላቅ ብሎ የሚነሳ ብልሀተኛ ንግሥት ናቸው፡፡
ከዓላማቸው ሸበርክ የማያወቁ፣ በጥበብ እና በብልሃት የተራቀቁ፣ ጥበብን እና ዕውቀትን በትልውድ ልብ ላይ ያፈለቁ እመቤት ናቸው ይሏቸዋል እቴጌ ምንትዋብን፡፡ ታምራት ወርቁ “የመማጸኛ ከተማ” በተሰኘው መጽሐፋቸው በጎንደር ዘመን ስማቸውን በወርቅ ያስጻፉ ታሪካዊት ሴት ናቸው፤ ኢትዮጵያ ላይ ብዙ አሻራ ትተው ያለፉ ንቁ፣ ኃይለኛ፣ ተራማጅ እና ጠንካራ መንፈሳዊት ሴት ነበሩ ብለዋቸዋል፡፡
የመሲህ ሰገድ በካፋ ባለቤት፣ የብርሃን ሰገድ ኢያሱ እናት፣ የአቤቶ ኢዮአስ አያት፣ የጎንደር እመቤት፣ የኢትዮጵያ ንግሥተ ነገሥታት፣ የጥበብ እናት ናቸው እቴጌ ምንትዋብ፡፡ እንደ እርሳቸው በዙፋን ያማረ፣ እንደእርሳቸው በዙፋን የተከበረ፣ እንደ እርሳቸውም ዘለግ ላሉ ዓመታት በዙፋን የኖረ ከየት ይገኛል ይሏቸዋል፡፡ የንግሥተ ነገሥታት ዘመናቸው ከባለቤታቸው መሲህ ሰገድ አጼ በካፋ ጀምሮ እስከ ልጅ ልጃቸው አቤቶ ኢዮአስ ይዘልቃልና፡፡
አሰግድ ተስፋዬ “ጎንደር የአፍሪካ መናገሻ” በሚለው መጽሐፋቸው ታላቋ ንጉሥት እቴጌ ምንትዋብ በዙፋን ስማቸው ብርሃን ሞገሳ ተሰኝተው ለንግሥትነት የሚያበቃውን የክብር ልብስ የለበሱ፣ የወርቅ አክሊል የጫኑ ንግሥተ ነገሥታት የተባሉ መሆናቸውን ጽፈዋል፡፡ እቴጌዋ ለ47 ዓመታት በዙፋን ተቀምጠው ሀገራቸውን ያሥተዳደሩ ብቸኛ መሪ ያደርጋቸዋል ይሏቸዋል፡፡
ንግሥቷ ውበታቸው ያማረ፣ አስታዋይነታቸው የሰመረ፣ ክብራቸው ከፍ ከፍ ያለ ነበርና ንጉሥ እና ንግሥት ማንገስ፣ ጥፋተኛን መውቀስ፣ ከጥፋቱ መመለስ እና ጀግናን ማወደስ የሚያውቁበት ጎንደሬዎች እንዲህ ሲሉ ተቀኙላቸው አሉ፡፡
“አሁን ወጣች ጀምበር
ተደብቃ ነበር
ደስ ይበልህ ጎንደር፡፡”
እኒያ ብልሆች በስም ምንተዋብ ተብለው፣ በምግባር አምረው የመጡትን ንግሥት ከጀምበር ጋር መሰሏቸው፤ የደስታ ማብሰሪያ አደረጓቸው፡፡ ተደብቀው የኖሩ፣ እንደ ጀንበር ያበሩ ናቸው አሏቸው፡፡
እቴጌ ምንትዋብ በዘመናቸው ሀገር በማስተዳደር፣ የተንገጫገጨውን በማደላደል፣ ደብር በመደበር፣ ገዳም በመገደም፣ አብያተ መንግሥታትን በማሳነጽ፣ ትውልድን በጥበብ በመቅረጽ፣ ሥልጣኔን በማስፋት አያሌ ታሪኮችን ሠርተዋል፡፡ በተዋበው የጎንደር አብያተመንግሥታት ቅጽር ውስጥ እጹብ የሚያሰኝ ቤተ መንግሥት አሠርተዋል፡፡ ከዋናው ቤተ መንግሥት ግቢ ባሻገር በሚገኝ የተዋበ ስፍራም ሌላ ቤተ መንግሥት እና የረቀቀች ቤተክርስቲያን አሠርተዋል፡፡ ቀጭን ፈታዮች እና ወይዛዝርት ግንብ የሚባል በእርሳቸው አማካኝነት የተሠራ ውብ አሻራም አላቸው፡፡ በቀጭን ፈታዮች እና ወይዛዝርት ግንብ ውስጥ ወይዛዝርቱን ሙያ ያስተምሩበት ነበር ይባላል፡፡ ይህም ሕንፃ ዶሮ 12 ብልት ተወጥቶላት፣ በቅመም ተከሽና ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበችበት ነው ይባላል፡፡
“አለው አለው እና ሲዘፈን በጎንደር
ንቅሳት ጌጥ እንጂ መች መለያ ነበር” እንዳለች ድምጸ መረዋዋ ጥርስን በንቅሳት የማስዋብ፣ ከውበት ላይ ውበት የመደራረብ ጥበብ እና አጊያጊያጥ የተጀመረውም በእኒሁ ንግሥት ዘመን እንደሆነ ይነገራል፡፡
እቴጌ ምንትዋብ ዙፋን ላይ ሲቀመጡ ኩሩ፣ ጀግና እና አስተዋይ ንግሥት፣ ወደ ደብር ሲያቀኑ ፍሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው እመቤት፣ ወደ እልፍኝ ሲገቡ ሴትነትን ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ በሙያ የተራቀቁ ሴት ናቸው፡፡ ሁሉን የተቸራቸው እመቤት፣ ሁሉ ያላቸው ንግሥት ናቸው እሳቸው፡፡
እቴጌዋ ለመቀመጫቸው አብያተ መንግሥታትን፣ ለክብራቸው መገለጫ ያማሩ እልፍኞችን፣ ለወይዛዝርቱ መማሪያ የተዋቡ ኪነ ሕንጻዎችን ብቻ አይደለም ያሠሩት፡፡ አድባራትን ማስደበር፣ ገዳማትን ማስገደምም ተክነውበታል እንጂ፡፡ በመናገሻዋ ከተማ በጎንደር ደብረ ጸሐይ ቁስቋም ማርያምን፣ በደንቢያ ቸመራ ቁስቋምን፣ ናርጋ ሥላሴን ውብ አድርገው አሠርተዋል፡፡ በአለፋ የሚገኘውን የሞገዳ ቤተ መንግሥትንም አሳድሰዋል፡፡
በዚያች በነገሡባት፣ በክብር እና በግርማ በዙፋን ላይ በኖሩባት፣ ባማረ ቤተ መንግሥት በተመላለሱባት፣ እልፍ በኋላቸው፣ እልፍ በግራቸው፣ እልፍ በቀኛቸው ባሰለፉባት፣ ዘመናትን አልፎ የሚያስጠራ ታሪክ በሠሩባት በመናገሻዋ ከተማ ጎንደር ያሠሯት የደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም፤ አሻራቸውን እና ረቂቅ ጥበባቸው እየነገረች ትኖራለች፡፡
አሰግድ ስለ ደብረ ጸሐይ ቁስቋም እና ስለ ቤተመንግሥታቸው ሲጽፉ “ ይህ ታሪካዊ ሥፍራ ለቀሃ ወንዝ የሚገብሩት የዛኒ ገደል እና አሙዛ ዥረቶች መሀል የሚገኝ ነው፡፡ ዛኒ ማለት ደጀን ማለት ነው፡፡ ይህ አውደ ግቢ የእቴጌ ምንትዋብን የጣት ቀለበት ጨምሮ አንድ ሺህ ወቄት ከአንድ ቀለበት ወርቅ ወጥቶበት በቀን አንድ ሺህ ሠራተኞች አምስት መቶ ሠሪ፣ አምስት መቶ አስተካካይ እየሆኑ የሠሩት ነው፡፡ ግቢዎቹም ከጥንት ጀምሮ የቤተክርስቲያኗ ግቢ እና የሺህ ወቄት ግቢ ተብለው ይጠራሉ” ብለዋል፡፡ ታምራት ወርቁ የመማጸኛ ከተማ በተሰኘው መጽሐፋቸው ደግሞ አንድ ሺህ ሠሪ አምስት መቶ አስተካካይ ሆነው ይሠሯት ነበር ብለዋል፡፡ በቀደመው ዘመን “ሺህ ሰሪ ሺህ አነዋሪ” እያሉ አበው እንደሚጠሩት ማለት ነው፡፡
ደብረ ፀሐይ ቁስቋም በግብጽ ሀገር ከምትገኘዋ እና ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በተሰደደችበት ጊዜ ልጇ ከዓለት ላይ ውኃ አፍልቆ ቅዱስ ቤተሰቡን ካጠጣበት እና የማርያም ገዳም ከተገደመበት ቦታ ስያሜዋ የተወሰደ ነው ይባላል፡፡ እቴጌዋ ይህችን ያማረች እና የተዋበች ሕንፃ ቤተክርስቲያን ሲያሠሩ የጣት ቀለበታቸውን ሰጥተው፣ እንቅልፍ ትተው እንደነበርም ይነገራል፡፡
የደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም ቤተክርስቲያን ቀዳሽ እና ታሪክ ነቃሽ ቄስ ገብረ ጻዲቅ እንዳለው ቤተክርስቲያኗ በ1733 ዓ.ም በዝነኛዋ ንግሥት እቴጌ ምንተዋብ አማካኝነት እንደታነጸች ነግረውኛል፡፡ አሰግድ ተስፋዬም ሕንጻ ቤተክርስቲያኗ በ1725 ዓ.ም ጀምሮ መታነጽ እንደጀመረች ጽፈዋል፡፡
ድንግል ማርያም በስደቷ ዘመን በግብጽ በቁስቋም አረፈች፡፡ እቴጌ ምንትዋብም የተሰደደችውን፣ ከፍጠራታት ሁሉ የላቀችውን እመቤት መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ቁስቋም ማርያምን አሳነጹ ይላሉ አበው፡፡ እቴጌዋ ወረኃ ጽጌ ስትፈጸም ለክብረ በዓል ወደ ቀድሞዋ ምሥር ወደ አሁኑ ግብጽ የሚሄዱ ምዕምናን ከእንግልት ለማዳን ያሳነጿት፣ ዳግማዊት ቁስቋም ትሆን ዘንድም የመረጧት ናትም የሚሉም አሉ፡፡ እቴጌ የእመቤታቸውን ታሪክ ለማስታወስ እርሳቸው ከዋናው ቤተ መንግሥት ራቅ ብለው ለመኖሪነት፣ አምላካቸውን ለማስገኛነት እና ለመማጸኛ ያስገነቧት ናትም ይሏታል፡፡ ይህች ያማረች እና የተዋበች ቤተ መቅደስ ከአርባራቱ የጎንደር አብያተክርስቲያናት መካከል አንደኛዋ ናት፡፡
ታምራት ወርቁ የመማጸኛ ከተማ በሚለው መጽሐፋቸው በቁስቋም ማርያም ቤተክርስቲያን በርካታ የእንቁላል ግንቦች አብረው መገንባታቸውን ጽፈዋል፡፡ የእንቁላል ግንቦችም የባሕታውያን መኖሪያ፣ የእንግዶች ማረፊያ፣ የምግብ ቤት አዳረሽ፣ የእቴጌዋ የጸሎት ቤት እና ሌሎች ያማሩ ኪነ ሕንጻዎች ናቸው፡፡
ይህች ያማረች ቤተ መቅደስ ጣሪያዋ በወርቅና በብር ተለብጣ እንደተሠራች ይነገራል፡፡ ጣሪያውም ተሰርቶ በተፈጸመ ጊዜ በቀይ ግምጃ ተሸብቦ ነበር ይባላል፡፡ ይህች የተዋበች ቤተ ክርስቲያን በኖራ፣ በሥንዴ ዱቄት፣ በእንቁላል፣ ሙጫ እና ጥሬ ጨው አምራ እንደተገነባች ይነገራል፡፡ ወይራ፣ ግማርዳ፣ ደንበቃ እና ዝግባ ደግሞ ለቤተ መቅደሱ መሥሪያነት የተመረጡ እንጨቶች ናቸው፡፡ እቴጌዋ ለቤተክርስቲያኗ ቀሳውስትን፣ ደባትራትን እና ጠባቆችን እንደመደቡላቸውም ይነገራል፡፡
ዘመናት አለፉ፤ ዘመናትም ተተኩ፤ መሐዲስቶች በጀግኖቹ ሥፍራ ወረራ ፈጽመው አብያተክርስቲያናትን አቃጠሉ፤ ገዳማትን በእሳት አነደዱ፤ ቀሳውስትን እና መነኮሳትን ገደሉ፡፡ በዚህም ዘመን ቃጠሎ ከደረሳባቸው የጎንደር አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት መካከል ደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም አንደኛዋ ናት፡፡ ደርቡሾች ዘርፈዋታል፤አውድመዋታልም፡፡ የረቀቀችውን አሻራ በእጅጉ አበጎሳቁለዋታል፡፡ ዳሩ የእቴጌን አሻራዎች፣ የገዘፉ ታሪኮች እና ጥበቦች ማጥፋት አልተቻላቸውም፡፡ ልጆቿ እንደገና ሠርተዋት፣ ነገሥታቱ አስውበዋት ታሪኳ ቀጠለ፡፡ ቤተ መቅደሷም እንደገና ተዋበች፡፡ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ውብ ኾና መታደሷንም ታሪክ ነቃሹ ነግረውኛል፡፡ ይህች ውብ ቤተክርስቲያን ታሪኳን እንደጠበቀች በዚህ ዘመንም ታድሳለች፡፡
በዚያች ያማረች ቤተክርስቲያን ውስ የበዙ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ ከፈረስ ቆዳ የተጻፈ ነገረ ማርያም፣ ገድለ ሰማዕታት፣ ድጓ፣ መስቀሎች፣ ጽዋዎች፣ የእቴጌዋ ማረፊያ አልጋቸው፣ ማንበቢያ አትሮንሳቸው እና ሌሎች የበዙ ቅርሶች ይገኙባታል፡፡
ወረኃ ኅዳር ብቶ በዓለ ቁስቋም በደረሰ ጊዜ ለኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ልዩ ነው። ነገሥታቱ፣ መኳንንቱ፣ መሣፍንቱ እና የጦር አበጋዞች፣ ወይዛዝርቱ እና ጎበዛዝቱ አጊጠው ወደ ቁስቋም ማርያም በክብር ያቀኑ ነበር፡፡
ዛሬም የነገሥታቱ የልጅ ልጆች፣ የነገሥታቱ ታሪክ ጠባቂዎች እና የመናገሻዋ ከተማ ነዋሪዎች በዓለ ቁስቋም በደረሰች ጊዜ ከአራቱም ንፍቅ እየወጡ ወደ ቁስቋ ይገሰግሳሉ፡፡ በዓለ ቁስቋምን ለማክበር የወደዱ ኢትዮጵያውያንም ወደ ቁስቋም ይመጣሉ እነሆ ቁስቋም ደርሳለች፤ ነጭ የለበሱ ምዕምናን በቁስቋም አጸድ ሥር ተሰባስበዋል፡፡ የጌታቸውን እናት የእመቤታቸው የማርያምን፣ የንግሥታቸውን የምንትዋብን ነገር እያሰቡ በዓሉን ያከብራሉ፤ በደስታ መጥተው፣ በደስታ ለዓመት ቀጠሮ ይዘው፣ አደራውንም ለአምላካቸው ሰጥተው በደስታ ይመለሳሉ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!