
አዲስ አበባ: ኅዳር 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጥቁር ሕዝቦች ማዕከል በኢትዮጵያ በቅርቡ ይፋ እንደሚኾን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል።መሥሪያ ቤቱ የፊታችን ህዳር 28/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይከፈታል ብለዋል። በአዲስ አበባ መሥሪያ ቤቱን እንዲያደርግ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ ሲሠራ መቆየቱ ይታወሳል፤ ማዕከሉ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መዲናነቱን የሚያጸና ትልቅ ተግባር ተደረጎ ይወሰዳል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለዚህ ማዕከል መቀመጫነት እንድታሸንፍ ያደረጋት የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ድርጅቶች መሥራች፣ የነፃነት ተምሳሌት እና የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን መሰረት ያደረገ ነው። ማዕከሉ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ቱርፋቶች ያመጡላታል ተብሎም ይታሰባል ብለዋል ቃል አቀባዩ።
የሱዳን የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልቡርሃን በኢትዮጵያ በነበራቸው ጉብኝት ኢትዮጵያ የሱዳናውያን ችግር በራሳቸው እንዲፈታ እንደምትፈልግ መገለጹን ተናግረዋል። ለዚህም ኢትዮጵያ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በአፍሪካ ኅብረት እና ኢጋድ በኩል መፍትሔ ማምጣት ይገባል ተብሏል። ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በነበራቸው ውይይትም ፍሬያማ እና የወንድማማችነት ውይይት አድርገዋል ብለዋል ቃል አቀባዩ።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በተያያዘ ያጋጠመው ችግር በተመለከተ አሚኮ የኢትዮጵያ ቢሮውን ዘግቶ እንደኾነ ያነሳውን ጥያቄ ቃል አቀባዩ ሲመልሱ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ድንገት በሚያጋጥሙ ችግሮች ግንኙነታቸው አይበላሽም፤ የተዘጋ ቢሮም የለም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አንዷለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!