
ባሕር ዳር: ኅዳር 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትን በተመለከተ በየደረጃው ከሚገኙ መሪዎች ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ በዘርፉ የሚገጥሙ ችግሮችን በአንድነት መፍታት እንደሚገባም ተነስቷል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሸው አሁንም የአቅርቦት ችግር እንዳይገጥመን በክትትል እና በትብብር መሥራት ይኖርብናል ብለዋል። “አርሶ አደሮች ሲፈልጉን መገኘት ይገባናልም” ነው ያሉት።
በግብዓት አቅርቦት ስርጭት ላይ ስርቆት እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ቢሮ ኀላፊው ይሄ እንዳይደገም መሥራት ይገባል ብለዋል። በሥርቆት ላይ የተሰማሩ አካላት መታረም እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
በግብዓት አቅርቦት ላይ የነበረው ችግር በክልሉ ለተፈጠረው የሰላም እጦት አንድ ምክንያት መኾኑንም አንስተዋል። ችግሩን ለመፍታት ደግሞ በቅንጅት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
የፌዴራል መንግሥት የግዥ ሥርዓቱን፣ የአቅርቦት ጊዜውን እና ሥርጭቱን በሚፈለገው ልክ ሠርቷል ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው በእኛ በኩል የሚጠበቅብን መሥራት ይገባናል ብለዋል። አቅርቦቱን በጊዜ ማዳረስ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር መኖርም የግብዓት አቅርቦቱን አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል። በእቅዶቻችን ላይ በመግባባት ለተፈፃሚነቱ መሥራት ይገባልም ነው ያሉት አቶ አጀበ።
ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ተግባብተን እንሥራ፤ በቅንጅት ካልሠራን ከፍተኛ ችግር ይገጥመናልም ብለዋል። ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የአቅርቦት ሥራው ስኬታማ እንዲኾን አርሶ አደሩን ማወያየት እንደሚገባም ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች ግብዓት አለን እንዴት እናሰራጨው ብንላቸው ለሥርጭቱ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋሉ ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!