
ባሕር ዳር: ኅዳር 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ተጠይቋል።
በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት እክል ከገጠማቸው ተቋማት ውስጥ የትምህርት ሴክተሩ አንዱ ነው።
በክልሉ ምሥራቅ፣ ምዕራብ እና ሰሜን ጎጃም ዞኖች አሁንም ድረስ ትምህር አለመጀመሩን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
በእነዚህ ዞኖች ውጭ በሚገኙ የክልሉ አካባቢዎች 60 በመቶ የአንደኛ ደረጃ እና 55 በመቶ የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች ብቻ በመማር ላይ ይገኛሉ። ለዚህ ደግሞ የጸጥታው ችግር አሁንም ሥጋት መኾኑን በምክንያትነት አስቀምጠዋል፡፡
ኀላፊዋ እንዳሉት በክልሉ በየጊዜው ሰላም በሚኾንባቸው አካባቢዎች ከጸጥታ መዋቅሩ እና ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ አየተሠራ ይገኛል።
የትምህርትግብዓት የማሟላት እና የመማር ማስተማር ሂደቱን የማስጀመር ሥራም እየተሠራ ነው ተብሏል።
ከዚህ በፊት የባከነውን የትምህርት ጊዜ ለማካካስ እንዲቻል ቢሮው የዓመቱን የትምህርት ሥርዓት እንደገና ለማሻሻል ጥናት እያደረገ እንደሚገኝም ኀላፊዋ ገልጸዋል።
በተለይም ደግሞ በዚህ ዓመት የክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተና ለሚወስዱ የ6ኛ፣ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የባከኑ ጊዜያትን በልዩ ሁኔታ ለመሸፈን ከመምህራን እና ርዕሰ መምህራን ጋር ውይይት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በተፈናቀሉ እና በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎችም መንግሥት ከሚሠራው ሥራ ባለፈ ረጅ ድርጅቶች፣ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች እና የልማት ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!